በሞዛምቢክ የሕገ መንግሥቱ ም/ቤት ገዢው ፓርቲ ባለፈው መስከረም መጨረሻ ላይ የተደረገውን ምርጫ እንዳነሸነፈ ማወጁን ተከትሎ ባለፉት 24 ሠዓታት ውስጥ በተደረገ ተቃውሞ ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ 21 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
አጨቃጫቂውን የምርጫ ውጤት ተከትሎ የሃገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ም/ቤት ገዢው ፍሬሊሞ ፓርቲ ማሸነፉን እንዳስታወቀ የተቃዋሚው መሪ ቬናሲዮ ሞንድላኔ ተቃውሞ እንዲደረግ ትላንት ጥሪ አድርገው ነበር።
ከእአአ 1975 ጀምሮ ላለፉት አምሳ ዓመታት በሥልጣን ላይ የቆየው የፍሬሊሞ ፓርቲ ባለፈው መስከረም መጀመሪያ ላይ በተደረገው ምርጫ አሸናፊ መሆኑ ከታወጀ ወዲህ በሃገሪቱ ለሳምንታት በርካታ ሕይወት የቀጠፈ ተቃውሞ ተደርጓል። እስከ አሁን 150 ሰዎች ከምርጫው ጋራ በተያያዘ ሁከት ህይወታቸው አልፏል። የገዢው ፓርቲ እጩ ዳንኤል ቻፖ አሸናፊ እንደሆኑ ቢነገርም፣ በአብዛኛው ወጣቶች የሆኑ የተቃዋሚው ቬናሲዮ ሞንድላኔ ደጋፊዎች ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሞ አድርገዋል።
በውጤቱ ቻፖ 65 በመቶውን ድምጽ እንዳገኙ ሲነገር፣ ሞንድላኔ ደግሞ 24 በመቶ እንዳገኙ ታውቋል።
ባለፉት 24 ሰዓታት 236 የሚሆኑ ጥቃቶች ተፈፅመው ሁለት ፖሊሶችን ጨምሮ የ21 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 13 ሲቪሎችና 12 ፖሊሶች ደግሞ መጎዳታቸውን የሃገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል።
በመዲናዋ ማፑቶ ሱቆች ሲዘረፉና ሲቃጠሉ የሚያሳዩ ምስሎች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ታይተዋል፡፡