በሞዛምቢክ ከሁለት ሳምንት በፊት በተደረገውና አጨቃጫቂ በሆነው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የገዢው ፍሬሊሞ ፓርቲ እጩ ዳንኤል ቻፖ ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዛሬ አስታውቋል።
ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው የፍሬሊሞ ፓርቲ እጩው ዳንኤል ቻፖ 71 በመቶውን ድምጽ ሲያገኙ፣ የተቀናቃኙ ፖዴሞስ ፓርቲ ወኪሉ ቬናንሲዮ ሞንዳኔ ደግሞ 20 በመቶ ድምጽ እንዳገኙ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
ተቀናቃኙ የምርጫውን ውጤት አለመቀበል ብቻ ሳይሆን አሸናፊው እርሳቸው መሆናቸውን በማስታወቃቸው እና ባለፈው ቅዳሜ ጠበቃቸውና አንድ ሌላ የተቃዋሚ አንቂ በመገደላቸው በሃገሪቱ ውጥረት መስፈኑ ተነገሯል፡፡
ጠበቃው ኤልቪኖ ዲያስ እና የማኅበራዊ አንቂው ፓውሎ ጉዋምቤ የተቃዋሚውን እጩ በመወከል የምርጫውን ውጤት በሕግ ለመሞገት በዝግጅት ላይ ነበሩ።
ተቃዋሚው ቬናንሲዮ ሞንዳኔ ለግድያው የፀጥታ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርገው፣ ቀጣዩ ዒላማ ምናልባትም እርሳቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ሞንዳኔ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረገ ጥሪ ሲያደርጉ፣ ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ፊሊፔ ኒዩሲ፣ "ኃይል የተቀላቀለበት የተቃውሞ ጥሪ ማድረግ የወንጀል ድርጊት ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አዲስ የተመረጡትና በመጪው ጥር ስልጣናቸውን የሚረከቡት ዳንኤል ቻፖ፣ ሞዛምቢክ ከፖርቹጋል ነፃ ከወጣች ወዲህ ተወልደው ፕሬዝደንት የሆኑ የመጀመሪያው ፖለቲከኛ ይሆናሉ።