ባለፈው ሳምንት ደቡባዊ አፍሪካዊቱን ሃገር ሞዛምቢክን በመታት ዝናብ አዘል ማዕበል ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ሞተዋል ሲሉ የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ተናገሩ።
ዋሺንግተን ዲሲ —
ሳይክሎን ኢዳይ በሰዓት ወደሁለት መቶ ኪሎ ሜትር ፍጥነት እየከነፈ የሞዛምቢኩዋን ደቡባዊ የህንድ ውቂያኖስ ጠረፍ ከተማ ቢይራን ከመታ በኋላ ወደምስራቅ ዚምባቡዌ እና ማላዊ አምርቷል ።
የሞዛምቢኩ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ ከመቶ ሺህ የሚበልጥ ህዝብ አደጋ ተደቅኖበታል ብለዋል። ዚምባቡዌ ውስጥም በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች የደረሱበት ጠፍቷል። እንድ ሺህ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትናንት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ሞዛምቢክ፣ ማላዊና ዚምባብዌ ውስጥ በከባዱ ማዕበል ቁጥሩ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው ለጉዳት መጋለጡን ገልጹዋል። የሚበዙት የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች እንደሆኑም አክሏል።