የዝንጀሮ ፈንጣጣ ዘረመል እየተጠና ነው

  • ቪኦኤ ዜና

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በፍጥነት እየተዛመተ ያለበት ምክንያት የቫይረሱ ዘረመል ተለውጦ እንደሆነ ለማወቅ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ቫይረስ በብዛት እንደሚታይባቸው አካባቢዎች “የኮንጎ ተፋሰስ ዝርያ”ና “የምዕራብ አፍሪካ ዝርያ” ተብለው የነበረ ቢሆንም የአካባቢዎቹ ዝና ከመጥፎ ነገር ጋር እንዳይቆራኝ በማሰብ የዓለም የጤና ድርጅት “ዝርያ አንድ”ና “ዝርያ ሁለት” ብሎ ባለፈው ዐርብ ሰይሟቸዋል።

ዝርያ ሁለቱ ቫይረስ ሁለት ንዑስ ዓይነቶች እንዳሉትና በዓለም ዙሪያ እየተዛመቱ ያሉትም እነሱ መሆናቸውን ድርጅቱ አክሎ ጠቁሟል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወይም መንኪ ፖክስ ካለፈው ግንቦት ጀምሮ ከተለመዱትና በብዛት ከሚታይባቸው የአፍሪካ አካባቢዎች ውጭ እየተዛመተ ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅት “አጣዳፊ ዓለምአቀፍ የጤና ሥጋት” ብሎ ባለፈው ሐምሌ 17 አውጆታል።

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዘጠና ሁለት ሀገሮች ውስጥ ከሠላሳ አምስት ሺህ በላይ ሰው አዳርሶ አሥራ ሁለት ሰው መግደሉን ዳብልዩ ኤች ኦ ጠቁሞ የቫይረሱ አዳዲስ ተጋላጮች በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ሪፖርት የተደረጉለት ከአውሮፓና ከአሜሪካ ንፍቀክበብ መሆኑንም አስታውቋል።