የሞልዶቫ ፕሬዝዳንት ማይያ ሳንዱ በትላንቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸንፈዋል። ሳንዱ የአውሮፓ ሕብረት አባል ለመሆን የዕጩነት ሥፍራ ለተሰጣት ሃገራቸው ወሳኝ መሆኑ በተነገረለት ምርጫ በሩሲያ የሚደገፉትን ተቃዋሚውን አሌክሳንደር ስቶያኖግሎን ለሁለተኛ ዙር በተካሄደው ምርጫ ነው ያሸነፉት።
ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የመራጭ ድምጽ መቆጠሩ በተገለጸበት የምርጫ ሂደት የሞልዶቫ ማዕከላዊ የምርጫ ኮሚሽን ሳንዱ ከአጠቃላዩ ድምጽ የ55 በላይ በመቶውን ማግኘታቸውን ይፋ አድርጓል። ተቀናቃኛቸው ከስቶያኖግሎ በአንጻሩ 45 በመቶውን የመራጭ ድምጽ ነው ያገኙት።
ምንም እንኳን ምርጫው በሩሲያ ጣልቃ ገብነት፣ በመራጭ ድምጽ መጭበርበር እና በመራጮች ላይ “የማስፈራራት ድርጊት ተፈጽሟል” የሚል ክስ ቢመሰረትም የሳንዱ ማሸነፍ አገራቸው የአውሮፓ ሕብረት አባላ ለመሆን ያሳደረችውን ተስፋ ሚያጎለብት ነው ተብሏል።