በሞቃዲሾ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

  • ቪኦኤ ዜና
ሞቃዲሾ ውስጥ ከሶማልያው ፕሬዚዳንት ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ከሚገኝ ምግብ ቤት ውጭ ዛሬ የደረሰ የመኪና ቦምብ ፍንዳታ በትንሹ ለ5 ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ሌሎች ዘጠኝ መቁሰል ምክንያት መሆኑ ተገለፀ።

የጥቃቱን ሰላባዎች ቁጥር ያስታወቁት የደኅንነት ባለሥልጣናትና የዳስላን ምግብ ቤት ባለቤት ናቸው። የምግብ ቤቱ ባለቤት ማምሻውን ለአሜሪካ ድምፅ የሶማልኛው አገልግሎት እንደገለፁት፣ ጥቃቱ የደረሰው መንገድ ላይ ቆሞ በነበረ አንድ ቦምብ የተጫነ መኪና አማካይነት ነው።

ምግብ ቤቱ በአብዛኛው የሚዘወተረው፣ ወደ ቤተ መንግሥቱ ከሚወስዱ መንገዶች አንዱን በሚጠብቁ ወታደሮች ነው ተብሏል። ኬላው ፍንዳታው ከደረሰበት ግማሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

“አንዳንዶቹ በፅኑ የተጎዱ 9 ሰዎችን ሆስፒታል አድርሰናል” ሲሉ የከተማዋ ብቸኛ ፈጥኖ ደራሽ የሕክምና አገልግሎት ሰጪ የአሚን አምቡላንስ ሠራተኞች ለአሜሪካ ድምፅ አስረድተዋል።

በዛሬው የመኪና ቦምብ ጥቃት 6 የመንግሥቱን ወታደሮች ገድለናል ያለው ነውጠኛው የአል ሻባብ ቡድን ኃላፊነት ወስዷል።

የዛሬው ጥቃት የደረሰው፣ ሁለት ያጥፍቶ ጠፊ መኪና ፍንዳታዎች ከአንድ ሳምንት በፊት በትንሹ 30 ሰዎችን ገድለው ሌሎች 140 ከጎዱ በኋላ ነው።