ኢትዮጵያ በዐዲሱ የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ ውስጥ የመካተት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

Your browser doesn’t support HTML5

ኢትዮጵያ በዐዲሱ የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ ውስጥ የመካተት ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

ኢትዮጵያ፣ በዐዲሱ የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ ውስጥ በመካተት ሽብርተኝነትን የመዋጋትና የሶማሊያን መንግሥት የመርዳት ፍላጎት እንዳላት አስታውቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፣ ዛሬ ዐርብ፣ ነሐሴ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋራ ያላትን ግንኙነት ለማጠናከርና ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን ለመፍጠር ያለመ ነው፤ ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፣ ባለፈው ታኅሣሥ 22 ቀን ከሶማሌላንድ ጋራ በተፈረመው አወዛጋቢው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት፣ ከሶማሊያ ጋራ ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እያሽቆለቆለ ባለበት ወቅት ነው፡፡

“የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች፣ በጠንካራ ወዳጅነት እና በማኅበረሰባዊ ግንኙነት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ በቀድሞ የግጭቶች ታሪክ መገደብ የለባቸውም፤” ያሉት ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋራ ያላትን ልዩነቶች “በሰላማዊ መንገድ መፍታት ጥረቷን ትቀጥላለች፤” ሲሉ አስታውቀዋል። ሶማሊያም፣ “የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረሩ አካላትን የማስተናገድ አካሔዷ ልታቆም ይገባል፤” ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ፣ ዐዲስ በሚቋቋመው የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት የተናገሩት አቶ ታዬ፣ “በርካታ ሀገራትም ይህን ሐሳብ ይጋራሉ፤” ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት ወታደሮችን ያዋጡበትን ነባሩን የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮን በምኅጻሩ አትሚስ በመተካት፣ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2025 ስምሪት ይቀበላል፤ በተባለው ዐዲሱ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ በምኅጻሩ አውሶም(AUSSOM) ውስጥ፣ ኢትዮጵያ እንዳትካተት ልታደርግ እንደምትችል ሶማሊያ መግለጿ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋራ የተፈራረመችውንና ሞቃዲሾ “ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው” የምትለውን የባሕር በር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ካልሰረዘች፣ በተልዕኮው እንድትካተት ፈቃዷ አለመኾኑን ነው ሶማሊያ የገለጸችው፡፡

አምባሳደር ታዬ በዛሬው መግለጫቸው፣ ዐዲሱ የሶማሊያ የሰላም ተልዕኮ፣ “ለኢትዮጵያ የደኅንነት ስጋት ምንጭ መኾን የለበትም፤” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ በዐዲሱ ተልዕኮ ውስጥ ባትካተት እንኳን፣ ደኅነነቷን የመጠበቅ ኃላፊነቷን ትወጣለች፤ ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ፣ በቱርክ-አንካራ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተደረገው ንግግር፣ አዎንታዊ መፍትሔ እያመጣ መኾኑን ጠቅሰው፣ “ንግግሩ በጥቂት ግለሰቦች ተንኳሽ ንግግሮች እና ለቀጣናው ዘላቂ ሰላም በማይመኙ ኃይላት ምክንያት ሊደናቀፍ አይገባም፤” ብለዋል፡፡

ጥቂት ግለሰቦች በማለት የገለጿቸውን አካላት ግን በስም ለይተው አልጠቀሱም።

በአንካራ፣ በሁለት ዙር የተደረጉ የተናጠል ውይይቶች ያለስምምነት መጠናቀቃቸው አይዘነጋም፡፡

ሶማሊያ፣ በአንካራው የተናጠል ውይይት ውጤት ላለማስመዝገቡ፣ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርጋለች። ፕሬዝዳንቷ ሐሰን ሼኽ መሐሙድ፣ ኢትዮጵያ “ሶማሊያን እንደ ነጻ ጎረቤት ሀገር እውቅና አልሰጠችም፤” ሲሉ፣ ለውይይቱ አለመሳካት ምክንያት ነው ያሉትን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ፣ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እስካላረጋገጠች ድረስ፣ ሶማሊያ በባሕር ጉዳይ ላይ እንደማትወያይም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ፣ ከዚኽ ቀደም በሰጡት አስተያየትም፣ ኢትዮጵያ፣ የሶማሊያን ፌዴራል መንግሥት ፈቃድ ሳታገኝ ከሶማሌላንድ ጋራ ውል በመፈራረም “የቆዩ ግጭቶች እንዲያንሰራራ እያደረገች ነው፤” በማለት ከሰዋል። ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ ብትቆጥርም፣ ራሷን ነጻ ሀገር አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊላንድ በበኩሏ፣ ከውጪ ሀገራት ጋራ በራሷ ስምምነቶችን መፈጸም እንደምትችል ትሞግታለች፡፡

ኢትዮጵያ፣ ራሷን ከሶማሊያ ነጥላ ነጻ ሀገር ነኝ ከምትለው ሶማሊላንድ ጋራ የተፈራረመችው የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ ካልኾነ፣ በማንኛውም መንገድ ሉዓላዊነቴን አስከብራለኹ፤ ያለችው ሶማሊያ፣ በዓባይ ውኃ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋራ አለመግባባት ውስጥ ከምትገኘው ከግብጽ ጋራ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት የመከላከያ ስምምነት መፈራረሟም ይታወቃል፡፡

ይኸው ስምምነት፣ “ፀረ ሽብርተኝነትን የመዋጋት ጥረትን ለማጎልበትና የመከላከያ ሠራዊታችን ሉዓላዊነታችንን የመጠበቅ ዓቅሙን ለማጠናከር ይረዳል፤” ሲሉ፣ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሞዓሊም ፊቂ ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱን ተከትሎ፣ ልዩ ልዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን የጫኑ ሁለት የግብፅ አውሮፕላኖች፣ ባለፈው ማክሰኞ ሶማሊያ መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ይህ በኾነ በማግስቱ ረቡዕ፣ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የግብጽን ስም ባይጠቅስም፣ “ሌሎች ተዋናዮች የአፍሪካ ቀንድ ክልልን ለማተራመስ ርምጃ ሲወስዱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም፤” ብሏል።

ሶማሊላንድም፣ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ባወጣችው መግለጫ፣ “የግብጽ ጦር በሶማሊያ መገኘቱን አጥብቄ አወግዛለኹ፤” ብላለች።

ርምጃውም፣ “ለሶማሊያ እና ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መረጋጋት እና ደኅንነት አሳሳቢ ነው፤” ስትልም፣ ራሷን ነጻ ሀገር አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊላንድ ገልጻለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ታዬም በዛሬው መግለጫቸው፣ “ሶማሊያ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚፃረሩ ኀይሎችን ከማስተናገድ ልትቆጠብ ይገባል፤” ሲሉ አሳስበዋል፡፡

“ያም ኾኖ፣ ኢትዮጵያ በሰላም ጥረቷ ትገፋለች፤” ነው ያሉት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡

የትኛውንም ሀገር ሳይጠቅሱ “ደንበር ላይ ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረግ” ያሉት ሙከራ እንዲቆምም አስጠንቅቀዋል። በአካባቢው፣ ለአሸባሪዎች እና ፀረ ሰላም ኀይሎች ምቹ ኹኔታ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን በዝምታ እንደማታልፍም ገልጸዋል።

በተያያዘ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ በልዩ መልዕክተኛ ደረጃ ለነበረው የሐርጌሳ ቆንስላ ጀነራል ጽሕፈት ቤት አምባሳደር የሾመች ሲኾን፣ ተሿሚው አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ሐሚቶ፣ ትላንት ኀሙስ ነሐሴ 23 ቀን፣ የሹመት ደብዳቤአቸውን ለሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ማቅረባቸውን፣ የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተከትሎ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ ሶማሊያ፥ በሐርጌሳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ እንዲዘጋ ትእዛዝ አስተላልፋ ነበር። ይኹን እንጂ ኢትዮጵያ፣ በሐርጌሳ ቆንስላ የነበሩትን ልዩ መልዕክተኛ ደሊል ከድር በአምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ተክታለች

ለፕሬዚዳንት ቢሂ የሹመት ደብዳቤ ያቀረቡትን ዲፕሎማት ይፋ ማዕርግ በተመለከተ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በይፋ የሰጡት አስተያየት የለም።