የገና በዓል ለማክበር ትናንት ሀሙስ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ተጓዦች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በየብስና በአየር መንቀሳቀሳቸው፣ የኦሚኮሮን የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ በሚገኝበት ጊዜ መሆኑ አሳሳቢ እንዳደረገው ተነገረ፡፡
በተለያዩ ከተሞች የምርመራ ስፍራዎች የተዘጋጁ ሲሆን እንደ ኒውዮርክ ባሉ ከተሞች በተለያዩ የመናፈሻ ስፍራዎች የምርመራ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
አንዳንድ ቦታዎችም ላይ የመንግሥት ሠራተኞችም በየጎዳናው ላይ ለሚተላለፉ መንገደኞች የኮቪድ-19 የራስ መመርመሪያ መሳሪያዎችን ሲያድሉ መታየታቸው ተዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ ምርመራውም ሆነ የኦምሪኮን ስጋት ተጓዦችን ከጉዞ እቅዳቸው ያላገዳቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ ኤርላይን፣ እኤአ በ2019 ከነበረው የተጓዥ መጠን ጋር ሲነጻጸር፣ 86 ከመቶዎቹን የመንገደኞች መጠን ማግኘቱን ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት እኤአ ከታህሳስ 19 አንስቶ እስከ ጥር 1 ድረስ በየቀኑ 5ሺ በረራዎችን የሚያካሂድ መሆኑንም አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ አውቶሞቢል ማህበርም የተጓዦቹ መጠን እኤአ በ2020 ከነበረው ተጓዥ 34 ከመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
እኤአ ከታህሳስ 23 እስከ ጥር ሁለት 109 ሚሊዮን ሰዎች በአየር፣ በየብስ በሌሎች የትራንስፖርት ዘዴዎች 50 ማይል ወይም ከዚያ በላይ ርቀት እየተጓጓዙ መሆኑን ማህበሩ አስታውቋል፡፡