የሱዳን ጦር ከተፋላሚው የፈጥኖ ደራሽ ጦር ጋራ ንግግሩን አቋረጠ

በተኩስ አቁም ወቅት ነዋሪዎች ቀለባቸውን ለመሸመት ዳቦ ቤት ተሰልፈው፤ ካርቱም፣ ሱዳን እአአ 5/27/2023

በተኩስ አቁም ወቅት ነዋሪዎች ቀለባቸውን ለመሸመት ዳቦ ቤት ተሰልፈው፤ ካርቱም፣ ሱዳን እአአ 5/27/2023

የሱዳን ጦር ሠራዊት፣ አገሪቱን በበላይነት ለመቆጣጠር ለሳምንታት ሲዋጋ ከሰነበተው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጋራ የጀመረውን ንግግር ማቋረጡን፣ የሠራዊቱ ቃል አቀባይ፣ ዛሬ ረቡዕ አስታውቋል፡፡

ውሳኔው፥ ሁለቱም ወገኖች፣ ሱዳንን ወደ ከፋ ቀውስ የከተታትን ግጭት እንዲያቆሙ ሲያደራድሩ ለቆዩት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ሳዑዲ አረቢያ፣ “ትልቅ ክስረት ነው፤” ተብሏል፡፡

የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ፣ ብርጋዴየር ጀነራል ናቢል አብደላ፣ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፣ ርምጃው፥ የፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች፣ የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነቱን በተደጋጋሚ በመጣሳቸው እና በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኙ ሆስፒታሎችንና የሲቪል መሠረተ ልማቶችን በተከታታይ ይዘው መቆየታቸውን በመቃወም የተወሰደ ርምጃ ነው፤ ብለዋል፡፡

አብደላ አክለውም፣ ተጨማሪ ርምጃዎች ላይ ከመወያየት በፊት፣ ሠራዊቱ፥ የተኩስ አቁሙ ዝርዝር ነጥቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረጋቸውን ማረጋገጥ ይፈልጋል፤ ብለዋል፡፡

ተፋላሚዎቹን ወገኖች ሲሸመግሉ ከቆዩት ሳዑዲ አረብያ ወይም ዩናይትድ ስቴትስ፣ ስለ ጉዳዩ ወዲያኑ የተሰጠ አስተያየት የለም፡፡

እስከ አሁን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል፣ በተለያዩ መንገዶች የተጣሱ ሰባት የተኩስ አቁም ስምምነቶች መደረጋቸው ተመልክቷል፡፡

የሱዳን ጦር ያሳለፈውን የንግግር ማቋረጥ ውሳኔ አስመልክቶ፣ የፈጥኖ ደራሹ ጦር በሰጠው ምላሽ፣ “የሳዑዲ አረብያንና የዩናይትድ ስቴትስን ተነሣሽነት፣ ያለምንም ቅድመ ኹኔታ እደግፋለኹ፤” ማለቱን፣ የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡