በሜድትራኒያን ባህር ከደረሱት የስደተኞች የጀልባ ጉዞ አደጋዎች መካከል እኤአ ሰኔ 14 ከደረሰው አሰቃቂ አደጋ በህይወት የተረፉትና ቤተሰቦቻቸው ከአንድ ዓመት በኋላ አሁንም መልስ እና ፍትህ እንደሚፈልጉ ተነገረ፡፡
በግሪክ ደቡብ ምዕራብ ዳርቻ በደረሰውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በሞቱበት በዚህ የጀልባ አደጋ 16 ጓደኞቹን ያጣው ግብፃዊው የኤሌትሪክ ባለሙያ ማህሙድ ሻላቢ ከትውልድ ከተማው ታላ የተረፈ ብቸኛው ሰው መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሻላቢ አሁንም በአቴንስ ጥገኝነት በመጠባበቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን ሌሎችም የጠፉ ዘመዶቻቸውን ሁኔታ ለማወቅ በየዕለቱ ከየቤተሰቦቻቸው ስልክ እንደሚደወልለት ገልጿል፡፡
የዛሬ ዓመት የደረሰው አደጋ በአውሮፓ ህብረት የፍልሰት ፖሊሲ ላይ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ እስካሁን ስለ ሁኔታው ይካሄዳል የተባለው ገለልተኛ ምርመራ ያልተጠናቀቀ ሲሆን ማንም ተጠያቂ አልተደረገም፡፡
የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ጀልባዋ የተገለበጠችው ከውሃ ውስጥ እየተጎተተች ባለበት ሁኔታው ውስጥ ነበር ቢሉም ባለሥልጣናት ግን ጀልባዪቱ በመንቀሳቀስ ላይ እንደነበረች ተናግረዋል፡፡
የግሪክ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ጀልባዪቱን ከአየር ላይ ይከታተላት እንደነበር ገልጾ ወደ ስፍራው ርዳታ ሰጭ መርከብ መላኩን አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ በመካከል ጀልባዋ በመስጠሟ በውስጧ ነበሩ የተባሉ እስከ 700 ከሚደርሱ ሰዎች መካከል በህይወት የተረፉት 104 ሰዎች እና የ82 ሰዎች አስክሬን ብቻ ሲገኝ የተቀሩት የደረሰቡት አልታወቀም፡፡
የግሪክ ባለሥልጣናት መጀመሪያ ተጠያቂ ያደረጓቸውን 9 ግብጻውያን በቁጥጥር ይዘው የተለቀቁ ሲሆን ምርመራው ወደ ባህር ዳርቻ ጠባቂዎቹ መዞሩ ተመልክቷል፡፡ የአካባቢው የባህር ኃይል ፍርድ ቤት እና የግሪክ ዕምባ ጠባቂ ተቋም ጉዳዩን እየመረመሩ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡