ወደ አውሮፓ በማቅናት ላይ የነበሩ 19 የሚሆኑ የቱኒዚያ ፍልሰተኞችን የጫነ ጀልባ ተገልብጦ አራቱ ሲገኙ 15ቱን ፍለጋ ላይ መሆኑን የአገሪቱ የባህር ድንበር ዘብ አስታውቋል፡፡
ጀልባው ሰኞ ማታ እንደሠመጠ ሲነገር፣ አንድ አሳ አስጋሪ አራቱን ፍልሰተኞች መታደጉን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል፡፡
ከጣልያኑ ላምፔዱሳ ደሴት 150 ኪሜ ብቻ ርቀት ላይ የሚገኘው የቱኒዚያ ባህር ዳርቻ፣ አደገኛውን ጉዞ በማድረግ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚፈልጉ ፍልሰተኞች ተመራጭ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ብቻ ከሰሃራ ግርጌ የመጡ 32 ፍልሰተኞች ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ ሰምጠዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና፣ ካናሪ በተባለው የስፔን ደሴት አቅራቢያ ከ100 የሚበልጡ ፍልሰተኞችን ዛሬ ማለዳ መታደጉን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
103 የሚሆኑት ፍልሰትኞች በሁለት ጀልባ በመሆን ወደ አውሮፓ በመሻገር ላይ ነበሩ፡፡ 18 ሴቶችና 49 ሕጻናት እንደሚገኙበት የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል። በዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የህክምና ዕርዳታ በማግኘት ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ባለፉት ወራት ብቻ 2ሺሕ 356 ፍልሰተኞች ካናሪ ደሴት ደርሰዋል።