Your browser doesn’t support HTML5
ሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ በማልታ ደሴት አቅራቢያ በሁለት የጀርመን ጀልባዎች ላይ ማረፊያ አጥተው የቆዩ አርባ ዘጠኝ ፍልሰተኞችን እንደሚያስተናግዱ የደሴቲቱ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዜፍ ማስካት ዛሬ አስታወቁ።
ስምምነቱ ከማልታ ጋር የተደረሰው ፍልሰተኞቹን እንደሚቀበሉ ስምንት የአውሮፓ ኅብረት ሃገሮች ከገለፁ በኋላ ነው።
የባሕር ቃፊር እና የባሕር 0ይን የሚባሉ ሁለት የጀርመን የሰብዓዊ አገልግሎት መርከቦች ናቸው ፍልሰተኞቹን ሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ ከአደጋ ያተረፏቸውና ያነሷቸው።
መርከቦቹ ወደ ላ ቫሌታ ወደብ መጠጊያ ፍቃድ በመከልከላቸው የራሷ የማልታ የጦር ጀልባዎች ናቸው ፍልሰተኞቹን ዛሬ ወደመሬት ያሸጋገሯቸው።
ፍልሰተኞቹ እጅግ እየቀዘቀዘ ባለው የአየር ሁኔታና በባሕሩም ጠባይ መነጫነጭ መብዛት ለቀናት ሲጉላሉና ሲሰቃዩ ከቆዩ በኋላ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ፖርቹጋል፣ አየርላንድ፣ ሮማንያ፣ ሉግዘምበርግና በፍልሰት ጉዳይ ላይ የከረረ አቋም የያዘችው ጣልያን እንኳ ሳትቀር እንደሚቀበሏቸው አሳውቀዋል። ከሌሎች ሃገሮች ጋርም ድርድሮች እየተካሄዱ መሆናቸው ተገልጿል።
ባለፈው ታኅሣስ መጨረሻ አካባቢ ሃገራቸው 249 ፍልሰተኞችን ማሳረፏን ያመለከቱት የማልታ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆዜፍ ማስካት እነርሱንም የሚያካትት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ከእንግዲህ ማንንም እንደማትቀበል ተናግረዋል።
ያለመፍትኄ የምታልፈው እያንዳንዷ ሰዓት የምታኮራቸው አለመሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ማስካት ጠቁመው “መፍትኄው ከአውሮፓ ሳይሆን ከኅብረቱ አባል ሃገሮች ተገኘ” ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ጣልያን ሕፃናትንና ወላጆቻቸውን ለማስተናገድ መወሰኗ በአጠቃላይ በፍልሰት ላይ እየወሰደች ያለችውን ጠንካራ እርምጃ አይለውጠውም ወይም አያቆመውም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ጁዜፔ ኮንቴ ብርቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፍልሰተኞቹ ባሕር ላይ እንዲህ ለተራዘሙ ቀናት ባሕር ላይ መንገላታታቸው “የአውሮፓን ገፅታ አያሳይም” ሲሉ የኅብረቱ የፍልሰት ጉዳዮች ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራሞፓውሎስ አውሮፓ ለመድረስ በመዘግየቷ የተሰማቸውን ቅሬታ ገልፀዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5