እስራኤል በዌስት ባንክ ባካሄደችው ጥቃት ቢያንስ ዘጠኝ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የአካባቢው የጤና ባለስልጣናት ዛሬ ረቡዕ ገለጹ።
ፍልስጤማውያኑ የተገደሉት ዋነኛው ጥቃትና ግጭት በተካሄደባቸው እስራኤል በያዘቻቸው የተለያዩ የጄኒን እና ቱባስ አካባቢዎች ነው፡፡
እስራኤል ሃማስ እና እስላማዊ ጂሃድን ጨምሮ በኢራን በሚደገፉ የሂዝቦላ ታጣቂ ቡድኖች ላይ የምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ጨምሯል፡፡
እኤአ ከጥቅምት 2023 ጀምሮ በዌስት ባንክ ከ640 በላይ ፍልስጤማውያን እና 19 እስራኤላውያን መሞታቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል እኤአ ጥቅምት 7 ቀን 2023 በሀማስ ከተያዙት 250 ታጋቾች መካከል ቃይድ ፋርሃን አልካዲ፣ የተባለ ሌላ አንድ ታጋች ማስለቀቋን ትላንት ማክሰኞ አስታውቃለች፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር የሚደረገው ጥረት የቀጠለ ሲሆን አሜሪካ፣ ካታር እና ግብፅ ታጋቾችን መልቀቅ እና ለጋዛ ሰብዓዊ ዕርዳታ መጨመርን ያካተተ እርቅ እንዲፈጠር ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።