“ጋዛ፣ ሊባኖስ እና ሱዳን አሁንም ድረስ እየተካሄዱ ባሉት ግጭቶች ከደረሰባቸው ውድመት ለማገገም አስርት አመታት ይወስድባቸዋል” ሲል የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓም በሰጠው መግለጫ የአገሮችን እድገት የተመለከተ ትንበያውን ዝቅ አድርጓል።
የእስራኤል ጦር ኃይል በጋዛ ሰርጥ በሃማስ፤ እንዲሁም ሊባኖስ ውስጥ በሄዝቦላ ላይ የከፈታቸው ጦርነቶች እና የሱዳኑ የእርስ በርስ ጦርነት ዘላቂ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ናቸው’ ሲል አስጠንቅቋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ አበዳሪ ተቋም አያይዞም “ግጭቶቹ የሚያደርሱት ጉዳት ፈጥኖ የማይሽር ዘላቂ ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ ነው” ብሏል።
አይኤምኤፍ እየተገባደደ ባለው የአውሮፓውያኑ 2024 ውስጥ ‘በመካከለኛው ምስራቅ እና በሰሜን አፍሪቃ ይዘገባል’ በሚል ሰጥቶት የነበረውን የእድገት ትንበያም ወደ 2 ነጥብ 1 በመቶ ዝቅ በማድረግ፤ ለዚህም ምክኒያቱ ጦርነቱ እና የነዳጅ ምርት መቀነስ ያስከተለው መሆኑን አመልክቷል።
የድርጅቱ የመካከለኛው ምስራቅ እና የመካከለኛው እስያ ጉዳዮች ድሬክተር ጂሃድ አዙር፣ ዛሬ ዱባይ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የያዝነው ዓመት በሰው ልጆች ላይ እጅግ አሰቃቂ ጉዳትና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ውድመት ያስከተሉ ግጭቶች የተስተናገዱበት ፈታኝ አመት ነበር” ብለውታል።