እስራኤል በተፈናቃዮች መጠለያ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 17 ተገድለዋል ተባለ

በሊባኖስ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ በምትገኘው ዳሂዬህ የእስራኤል የአየር ጥቃት ከደረሰበት ሥፍራ ጭስ ሲወጣ ይታያል፤ እአአ ኦክቶበር 24/2024

እስራኤል ተፈናቃዮች በተጠለሉበት አንድ ት/ቤት ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 17 ሰዎች መሞታቸውን የፍልስጤማውያን የጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። በጥቃቱ ሌሎች 42 ስዎች መጎዳታቸውም ታውቋል።

የእስራኤል ሠራዊት በበኩሉ የሃማስ ታጣቂዎች ትምህርት ቤቱን እንደ ማዘዣ ጣቢያ ሲጠቀሙበት ነበር ብሏል። ሠራዊቱ ለዚህ ማስረጃ እንዳላቀረበ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።

ለለፉት ሁለት ሳምንታት እስራኤል በምድርና ከአየር በምትፈጽመው ድብደባ ምክንያት አሳሳቢ የሰብዓዊ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉ የጤና ሠራተኞች እያስጠነቀቁ ነው።

በዛሬው የአየር ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ 13 ሕፃናትና 18 ሴቶች እንደሚገኙበት የሆስፒታል ሰነዶች አመልክተዋል።

እስራኤል ላለፉት ጥቂት ወራት በተፈናቃይ መጠለያነት በማገልገል ላይ ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ ጥቃቷን የጨመረች ሲሆን ትምህርት ቤቶቹ ለሐማስ የማዘዣ ጣቢያነት እያገለገሉ ነው ብላለች፡፡ እስራኤል ለዚህ ማስረጃ እንዳላቀርበችና ጥቃቶቹ በአብዛኛው ሴቶችና ሕፃናትን እንደሚገድሉ የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል።