አዲስ ጠለፋ በመተማ

Your browser doesn’t support HTML5

አዲስ ጠለፋ በመተማ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ውስጥ በሣምንቱ መጀመሪያ ቢያንስ ሃያ ስምንት ሰዎች በታጣቂዎች ተጠልፈው ታግተዋል” ሲሉ ቤተሰብ ነን የሚሉና የአካባቢው ነዋሪዎች ለቪኦኤ ተናግረዋል።

መቃ ቀበሌ በሚገኘው ቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የነበሩ 12 የአብነት ተማሪዎች ታፍነው መወሰዳቸውንና ጠላፊዎቹ ለየቤተሰቦቻቸው ስልክ እየደወሉ የማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸውን አንድ አገልጋይ ገልፀዋል።

በዚያው ቀን ከሰዓት በኋላ ከገንዳ ውኃ ከተማ ወደ ጎንደር በሚወስደው መንገድ ላይ ሹፌሩን ጨምሮ 16 የሚሆኑ የሚኒ በስ ተሳፋሪዎች "ደረቅ አባይ" በሚባል ቦታ ላይ መጠለፋቸውንና የእነርሱም ቤተሰቦች በተመሳሳይ ሁኔታ ማስለቀቂያ ገንዘብ መጠየቃቸውን የታጋች ቤተሰብ ነኝ ያሉ አመልክተዋል።

በመተማ ወረዳና በአካባቢው እየተባባሰ የመጣው ጠለፋና እገታ እንዳሳሰባቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች እየተናገሩ ነው።

ጠላፊዎቹ “ከቅማንትም ሆነ ከአማራ ወገን ያልሆኑ ሽፍቶች ናቸው” ሲሉ የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳለአምላክ ስመኘው ገልፀው እንዲህ ዓይነቱ ጥቃት እየበዛ መምጣቱ ፓርቲያቸውን እንደሚያሳስበው ተናግረዋል።

በአካባቢው በቂ የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አለመመደቡንና ነዋሪዎች ባልታወቁ ሰዎች እየታገቱና እየተገደሉ እንደሆነም ገልፀዋል።

ከአካባቢው ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡