መሠረት ደፋር በሞናኮ፤ የኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች ጎርፍ በሕንድ

  • ሰሎሞን ክፍሌ
መሠረት ደፋር የዓለም አምስተኛዋ ምርጥ አትሌት ናት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሴት አትሌቶች በሕንድ ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ወጡ፡፡

ኬንያው ዴቪድ ሩዲሻ እና የክሮኤሽያዋ ተወላጅ ብላንካ ቭላሲች የዓመቱ የዓለም ምርጥ አትሌቶች ተባሉ። የሽልማቱ ሥነ ሥርዓት በተካሄደባት በሞናኮ ከተማ የተገኘውን ፍቅሩ ኪዳኔንና ዕጩ ተወዳዳሪዋን አትሌት መሠረት ደፋርንም የስፖርት ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢው ሰሎሞን ክፍሌ አነጋግሯል።

በኒው ዴልሂ ሕንዱ ማራቶን ደግሞ በሴቶቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ተከታትለው በመግባት ታሪክ መሥራታቸውን ተሰምቷል። በወንዶቹም ድል ተቀዳጅተዋል ይላል ዘገባው።

*******

የ 21 ዓመቱ ሩዲሻ ዘንድሮ በ 800 ሜትር ሩጫ ውድድር ሁለቴ የዓለምን ክብረ ወሰን ሠብሯል። በመጀመሪያ በርሊን ላይ በሌላው ኬንያዊ በዊልሰን ኪፕኬተር ለ13 ዓመታት ተይዞ የቆየውን ሬከርድ በመስበር 1 ደቂቃ ከ41 ነጥብ 09 ሴኰንድ ገብቷል። ከአንድ ሣምንት በኋላ ሪየቲ ላይ 1 ደቂቃ ከ41 ነጥብ 01 ሴኰንድ በመጨረስ የራሱን ክብረ ወሰን አደሰ። በርቀቱም በ12 ውድድሮች አሸንፏል። በአፍሪቃም ሻምፒዮን ሲሆን በዚሁ ርቀት ክሮኤሽያ ስፕሊት ከተማ በተካሄደው አህጉራዊ ውድድር ቀድሞ በመግባት ዋንጫውን አንስቷል።

ብላንካ ቭላሲች ደግሞ ሁለት ሜትር ከ08 በመዝለል በታሪክ ሁለተኛዋ የከፍታ ዝላይ አትሌት ናት።

ለመጀመሪያ ጊዜም የአውሮፓ ሻምፒዮን ሆናለች። ከ14 ውድድሮች በ12ቱ አሸንፋለች።

በሴቶቹ ዘንድሮ ምርጥ የዓለም አትሌት ለመሆን ዓለምአቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በመጨረሻ ካቀረባቸው አሥር አትሌቶች ኢትዮጵያዊቷ መሠረት ደፋር አንዷ ነበረች። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ደጋፊዎቿ እንድትመረጥ ድምፅ ሰጥተዋታል፡፡ ዘመቻው ቀላል አልነበረም።

በሦስትና አምስት ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድሮች ታዋቂዋ መሠረት ደፋር በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዮና በአምስት ሺህ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ ናት።

በ2006 እና በ2007 በርቀቱ የዓለምን ሬከርድ እስከ 2008 ይዛ ከቆየች በኋላ የተነጠቀችው በገዛ አገሯ ልጅ በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ነው።

በ2004 አቴንስ ኦሊምፒክ በ 5000 ሺህ ወርቅ፥

በ2007 ኦሳካ ጃፓን የዓለም ሻምፒዮና ውድድር በ 5000 ሺህ ወርቅ፥

በ2004 ቡዳፔሽት፥

በ2006 ማስክቫ፥

በ2008 ቫሌንሲያ፥

በ2010 ዶሃ - በአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና በ3000 ሺህ ሜትር በሁሉም የወርቅ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች።

በ2006 ባምቡስ የአፍሪቃ ሻምፒዮና በ5000 ሺህ ወርቅ፥

በ2003 አቡጃ፣ ናይጄሪያና በ2007 አልጀርስ ላይ በተካሄዱ የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በ5000 ወርቅ............ ዝርዝሩ ብዙ በጣም ብዙ ነው በመሠረት ደፋር የሜዳልያ ቤተ መዘክር የተደረደረው የወርቅ፥ የብርና የነሐስ ሜዳልያ ስብስብ።

ዛሬ ጠዋት ፈረንሳይ ሀገር ሆቴል ክፍሏ ውስጥ እንዳለች በስልክ አግኝቻታለሁ።

እውቁ የስፖርት ጋዜጠኛና ደራሲ ፍቅሩ ኪዳኔ እንደሁ ጡረታም ወጥቶ ይህን ከመሰለው ዓለምአቀፍ መድረክ አይርቅም። እንደ ሁሌውም በክብር እንግድነት ተጋብዞ በሞንቴ ካርሎው የዓመቱ ምርጥ የዓለም አትሌት ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቷል።

ወደ ሌላ አትሌቲክስ ስፖርት ዜና ስናልፍ ኒው ዴልሂ ሕንድ ከተማ ትላንት ዕሁድ በተካሄደው የሴቶቹ ግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር በአትሌት አሰለፈች መርጊያ የተመራው ስኳድ - ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ተከታትሎ በመግባት ታሪክ ማስመዝገቡን እናገኛለን።

በ68 ደቂቃ ከ35 ሴኰንድ አንደኛ አሰለፈች መርጊያ፥ መሪማ መሐመድ ሁለተኛ፥ ውዴ ይመር ሦስተኛ፥ አበሩ ከበደ አራተኛ፥ አፀደ ባይሳ አምስተኛ፥ መስታወት ቱፋ ስድስተኛ፥ ፈይሴ ቦሩ ሰባተኛ። በእውነትም አስደናቂና አስደሳች ውጤት ነው።

በወንዶቹም ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል።

ከአንደኛው ኬንያዊ ከጆፍሬይ ሙታዪ ቀጥሎ በሁለተኛና ሦስተኝነት ተከታትለው የገቡት ሌሊሣ ደሲሳ እና ያዕቆብ ያርሦ ናቸው።

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ