በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያን የጎበኙት፣ የጣልያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ መሎኒ፣ ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፍ እና ስደትን ለማስቆም የሥልጠና ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡
ባለፈው ዓርብ፣ ኢትዮጵያ ገብተው የነበሩት የጣልያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ፥ በስደተኞች፣ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና በኹለቱ አገሮች መሀከል ስለሚኖረው የኢኮኖሚ ትብብር መነጋገራቸውን፣ የአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሓሳን ሼክ ሞሐሙድ በተገኙበት ባለፈው ቅዳሜ፣ የሦስትዮሽ ውይይት መካሔዱ ሲታወቅ፣ ጣልያን፥ ለአካባቢው ሰላም እንዲሁም ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ ጋራ ስለሚደረገው ቀጣይ የኢኮኖሚ ትብብር ልዩ ትኩረት እንደምሰጥ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡
ቀኝ ዘመሙ የጣልያን መንግሥት፣ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ባለው የፍልሰተኞች ቁጥር ምክንያት፣ ስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ያወጣ ሲኾን፣ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ አገሮች፣ ወደ ጣልያን የሚደረገውን ፍልሰት ለማስቆም ጠቃሚ ሚና እንደሚጫወቱ መሎኒ አመልክተዋል፡፡
ባለፉት አራት ወራት ብቻ፣ 31 ሺሕ የሚኾኑ ፍልሰተኞች፣ የሜዲትራንያን ባሕርን ተሻግረው ወደ ጣልያን ገብተዋል፡፡