አርባ የሚሆኑ አባላትን የያዘው የኃይማኖት መሪዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ቡድን፤ ከትላንት በስቲያ ወደ መቀሌ ከተማ አምርተው ትላንትና እና ዛሬ በተለያየ መልኩ ከክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ባለሞያዎች፣ከመቀሌ ከተማዋ የተወሰኑ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ለትግራይ ክልል አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልግ፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ እና በአማራ ክልል የተያዘው የትግራይ ቦታዎች እንዲለቀቁ እንዲደረግ ከተሳታፊዎች ጥያቄ መቅረቡን የጊዜያዊ አስተዳደሩ የኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የትግራይ የሃይማኖት መሪዎች በውይይቱ ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊገኙ እንዳልቻሉ አንድ ስማቸውን እና ማንነታቸውን መግለፅ ያልፈለጉ የትግራይ የሃይማኖት መሪዎች አባል ለአሜሪካ ድምፅ ገልፀዋል።
በሌላ በኩል የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሎዎች እና ሌሎች አካላት ከዚህ ቀደም ጦርነቱ ሲካሄድ ደግፈው አሁን ለእርዳታ በሚል ወደ ከተማው መግባታቸውን ነዋሪው እንዲቃወመውና ለሦስት ቀናት በሚዲያ እና በመልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች አማካኝነት ጥሪ በቀረበ የአድማ ጥሪ መሰረት ትላንት እና ዛሬ በመቀሌ ከተማ የሚገኙ አብዛኞቹ ንግድ ቤቶች መዘጋታቸውን፣ እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎ መንገዶች ተዘግተዉ ጎማዎች ሲቃጠሉ እንደነበር ታውቋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ እቴነሽ ንጉሴ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፤“ትግራይ የሃገር ሽማግሌዎቹም ሆነ የኃይማኖት አባቶቹ ወደ መቀሌ የመጡት ትግራይ ክልል ያለችበትን ሁኔታ ተረድተው የመፍትሔ አካል ለመሆን ነው። በዛም መሰረት ያሉትን ችግሮች በሚገባ ተረድተዋል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ዋናው የጉዞው ዓላማ ችግሮችን ተጋግዞ መፍታት እንዲቻል በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል። ቡድኑ ችግሩ ከመከሰቱ አስቀድሞም ሲሠራ የነበረ መሆኑን ገልፀው፤ በአሁኑ ሰዓት ለትግራይ ክልል ሕዝብ የሚያስፈልገው የተፈጠረውን የሰብዓዊ ቀውስ ማስተካከል እና እንዳይባባስ ተባብሮ መራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5