እስር ቤቱን ባወደመው የየመኑ የአየር ጥቃት ብዙ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

  • ቪኦኤ ዜና
ሰዳ በሚገኝ እስር ቤት አየር ድብደባ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል እስር ቤት ወድሟል፤ እአአ ጥር 21/2022

ሰዳ በሚገኝ እስር ቤት አየር ድብደባ የሞትና የመቁሰል አደጋ ደርሷል እስር ቤት ወድሟል፤ እአአ ጥር 21/2022

የመን ውስጥ በሚገኝ አንድ እስር ቤት ላይ ትናንት ምሽት በተካሄደውና "ዘግናኝ ነው" በተባለ የአየር ጥቃት በርካቶች መሞታቸውን ወይም ደብዛቸው መጥፋቱን የረድኤት ድርጅት ሠራተኞችን የጠቀሰው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

የሁቲ አማፂያን ዋነኛ ይዞታ ነው በተባለው ሳዳ ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ከወደመው የህንፃ ፍርስራሽ ውስጥ በእርዳታ ሠራተኞች የተለቀሙ በርካታ አስክሬኖች መከመራቸውን የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በአማጽያኑ መለቀቁ ተገልጿል፡፡

በተለቀቀው የቪዲዮ ምስል ከወደመው የህንጻ ፍርስራሽ ስር ከጥቃቱ የተረፉሰዎች፣ በስፍራው የወደቁ አስክሬኖችን በሀዘን ሲመለከቱ የሚያሳይ እንደሚገኝበት ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

በሳኡዲ አረብያ የሚመራው የመንግስት ደጋፊዎች ህብረት የቴሌኮኒሙኔክሽን ጣቢያውን ያወደሙት በመሆኑ በመላው የመን የኤንተርኔት አገልግሎት መቋረጡም ተመልክቷል፡፡

በእስር ቤቱ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከቆሰሉት ውስጥ የሳዳ ሆስፒታል ሊቀበል የቻለው 200 እስረኞችን ብቻ በመሆኑ ከዚያ በላይ ያሉትን መቀበል እንዳልቻሉም ዘገባው አመልክቷል፡፡

በየመን የድንበር የለሽ ሀኪሞች ተወካይ በርካታ አስክሬኖች ቁስለኞችና ያሉበት ሁኔታ ያልታወቁ ሰዎች እንደሚገኙ ለኤፍ ፒ ተናግረዋል፡፡

ጥቃቱ የተሰነዘረው በኢራን የሚደገፉ የሁቲ አማጽያን ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬት በላኩት የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸው ከተነገረ አምስት ቀን በኋላ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ተባበሩት አረብ ኤምሬት በደረሰባት ጥቃት ላይ እንዲነጋገር በጠራችው መሰረት የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ለዛሬ አርብ ስብሰባ ጠርቶ እንደነበር ታውቋል፡፡

የተባበሩት አረብ ኤምሬት በየመን ጦርነት የተሳተፈው የሳኡዲ መሩ አገሮች ህብረት አባል መሆንዋ ይታወቃል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት እስካለፈው የ2021 ዓመት መጨረሻ ድረስ በ እስከዛሬው የየመንጦርነት 377ሺ ሰዎች መሞታቸውን አመልክቷል፡፡