በማሊ ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ቡድኖች፣ በማሊ ወታደራዊ አገዛዝ እንዲያበቃ እና በአስቸኳይ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ እንዲደረግ ጠይቀዋል። እ.አ.አ በ2020 እና 2021 በተከታታይ መፈንቅለ መንግስት ከተካሄደ በኋላ ማሊ በወታደራዊ ሁንታ ስትተዳደር ቆይታለች፡፡
ከ.እ.አ.አ 2022 ጀምሮ በኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሚመራው ሁንታ፣ የሽግግሩ ወቅት ባለፈው ሰኞ እንደሚያበቃና ምርጫ እንደሚያደርግ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ላልትወሰነ ጊዜ እንደተላለፈ አስታውቋል። ሁንታው ወደፊት ምን ለማድረግ እንዳቀደ አለማስታወቁ አሳሳቢ እንደሆነ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
የፖለቲካ ፖርቲዎቹና ሲቪል ቡድኖቹ ለሁለት ተከፍለው ባወጡት መግለጫ፣ ሁንታው ሁሉንም የሚያካትት ውይይት እንዲደረግ እንዲፈቅድ እንዲሁም የሽግግር ወቅቱ ባለፈው ሰኞ በማክተሙ ምርጫ እንዲካሄድ ጠይቀዋል።
የተቃዋሚዎች ድምፅ በማሊ ብዙም የማይሰማ ሲሆን፣ አንድ አዲስ የተቃዋሚ ቅንጅት “ሕዝቡን እንዳይረብሽ” በሚል ባለፈው ሳምንት ታግዷል። ቅንጅቱ ሁንታውን እጅጉን የሚነቅፍ ሲሆን፣ ከአልቃይዳ እና ከእስላማዊ መንግስት ጋራ ግንኙነት ባላቸው ኃይሎች ከአስር ዓመታት በላይ ለታመሰችው ሃገር “አዲስ መንገድ” ያስፈልጋታል ሲል ሃሳብ አቅርቧል፡፡
ካለፈው ታህሳስ ወዲህ በመልካም አስተዳደር እና ምርጫን በመሰሉ መስኮች የሚሰሩ ቢያንስ አራት ድርጅቶች እንዲከስሙ መደረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።