ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒዤር የጋራ ፓስፖርት ሊጠቀሙ ነው

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የማሊ ወታደራዊ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ

ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒዤር በቅርቡ አዲስ የባዮሜትሪክስ ፓስፖርት በሥራ ላይ እንደሚያውሉ የማሊው ወታደራዊ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ትላንት እሁድ አስታውቀዋል።

ሦስቱ የሳህል ቀጠና ሃገራት ከእ.አ.አ 2020 ጀምሮ በተከታታይ የተፈጸሙ መፈንቅለ መንግስቶችን ተከትሎ በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ይገኛሉ።

ሦስቱ ሃገራት ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ከቀጠናው የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) ተገንጥለው በመውጣት ‘የሳህል ሃገራት ትብብር’ መሥርተዋል። ሃገራቱ ከቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ፈረንሣይ ጋራ የነበራቸውን ግንኙነት በማቋረጥ ፊታቸውን ወደ ሩሲያ አዙረዋል። ኤኮዋስ በፈረንሣይ የሚዘወር ነው ሲሉም ክስ አሰምተዋል።

ባለፈው ሐምሌ ደግሞ ‘የሳህል ሃገራት ኮንፌዴሬሽን’ በሚል ግኙነታቸውን አጠናክረው፣ 72 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ የሚኖርበትን ቀጠና በመጀመሪያው ዓመት ማሊ እንደትመራ ተስማምተዋል።

በቀጣዮቹ ቀናት አዲስ የባዮሜትሪክስ ፓስፖርት እንደሚታደልና ይህም በቀጠናው የጉዞ ሰነድ አሰጣጥን እነሚያሳልጥ አሲሚ ጎይታ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አሜሪካ በኒዤር የነበሯትን ወታደሮች አስወጥታ ማጠናቀቋን ዛሬ አስታውቃለች፡፡ አሜሪካ ጦሯን ያስወጣችው ኒዤር ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት ነው። በቀጠናው የሚገኙ እስላማዊ አክራሪዎች ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ለማገዝ በሚል አሜሪካ በኒዤር አንድ ሺሕ የሚሆኑ ወታደሮችና የድሮን መሠረት ነበራት፡፡