በማሊ የእስላማዊ ነውጠኞች ጥቃት ቀጥሏል

ፎቶ ፋይል፦ ባማኮ፤ ማሊ

በማሊ በእስላማዊ ነውጠኞች የደረሰ ነው በተባለ ጥቃት 64 ሰዎች ሕይወታቸውን ባጡ ማግስት፣ ዛሬ ዓርብ ደግሞ በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ባለ ወታደራዊ ሠፈር ላይ አጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት አድርሰዋል።

ሠራዊቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ባወጣው መግለጫ፣ የወታደራዊ ሠፈሩ የአየር ማረፊያ “ውስብስብ” ጥቃት ደርሶበታል ብሏል።

ዝርዝር መረጃ ከመግለጽ የተቆጠበው ሰራዊቱ፣ “ጥቃቱን በመገምገም እና የመልስ እርምጃ በመስጠት ላይ” መሆኑን ገልጿል፡፡

በቀጠናው ሶስት የሳህል ሀገራትን ያበጠው የጂሃዲስቶች ጥቃት፣ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከማሊ መውጣቱን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ተባብሷል።

አንድ የአየር ማረፊያው ሠራተኛ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፣ የዛሬው ጥቃት በሁለት መኪኖች ላይ በተጠመዱ ፈንጂዎች የተካሄደ ሲሆን፣ የትኩስ እሩምታም ተከትሏል።

አንድ ቀን ቀደም ብሎ በአንድ ጀልባ እና የጦር ሰፈር ላይ በደረሰ ጥቃት፣ 45 ሲቪሎች እና 15 ወታደሮች ተገድለዋል።

ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነት ወስዷል።