በቆሎ ናረ

  • እስክንድር ፍሬው
በኢትዮጵያ የበቆሎ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ተጠቃሚዎችና የችርቻሮ ነጋዴዎች መማረራቸውን ይናገራሉ።

አዲስ አበባ መሣለሚያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቆሎና ሌሎች የጥራጥሬ እህሎች የጅምላና የችርቻሮ ንግድ በስፋት ይካሄድባቸዋል። ዋጋው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨምረ መምጣቱ ግን ተጠቃሚዎችን ያማረረ ይመስላል። ከፈረንሳይ ለጋሲዮን መሣለሚያ ድረስ የመጡት ወይዘሮ ከተጠቃሚዎች አንዷ ናቸው።

“ግንቦት ላይ ኪሎው 5ና 6 ብር ነበረ። አሁን 7.50 እየሆነ ነው። የአንድ ብር ለውጥ አገኝ እንደሆነ ብየ ነበረ እዚህ ድረስ የመጣሁት።”

አንዳንድ ተጠቃሚዎች ግን በዋጋው መጨመር ቢማረሩም ከእግዜብሔር ጋር ነው መነጋገር የሚሻለው በማለት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል። በቆሎ ከሚቸረችሩ ነጋዴዎች መካከል አንዱ የበቆሎ ዋጋ በሁለት ዓመት ውስጥ በእጥፍ መጨመሩን ይናገራሉ።

“የበቆሎ ዋጋ ወደ ላይ መውጣቱን ይቀጥላል። ካቻምና ወደ ሁለት መቶ አካባቢ ነበረ። ዘንድሮ 600 ቤት ገብቷል። ለዋጋው መጨመር ምክንያቱን አናውቅም። ባመጡልን ዋጋ መሠረት እንቸረችራለን።”

ለ8 ዓመታት በበቆሎ ንግድ ላይ የቆዩት የችርቻሮ ነጋዴ ባጭር ጊዜ ውስጥ እንኳ የዋጋ ጭማሪ መካሄዱን ይናገራሉ።

“ከጥቂት ወራት በፊት ኩንታሉ 500 ብር ነበረ፤ አሁን ወደ 650 ብር ገብቷል። ወደ 150 ብር ጭማሪ አሣይቷል። የጨመረበት ምክንያት ወደ ውጪ ስለሚወጣ መሰለኝ። ፍላጎቱ ስለጨመረና አቅርቦቱ ስላነሰ፤ ሁለቱ አልተመጣጠኑም። ይሁን እንጂ ዋጋ የሚጨምርባቸውና የሚቀንስባቸው ወቅቶች አሉ። ለምሣሌ በታህሣስና በጥር የመቀነስ አዝማሚያ ያሳያል። በክረምት ወራት ግን እጥረት ስላለ ይጨምራል።”

በጉዳዩ ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ምላሽ ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። መንግሥት የዋጋ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው ባወጣቸው የመሠረታዊ ፍጆታዎች ዝርዝር ውስጥ በቆሎ አልተካተተም።

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡