የሜይን ግዛት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ትራምፕን ከቅድመ ምርጫ ውድድር አገዱ

  • ቪኦኤ ዜና

የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ሜይን ግዛት የውጭ ግንኙነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ሼና ቤሎውስ፣ የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግዛቲቱ ውስጥ ፓሪያቸውን ወክለው በመጪው ምርጫ ለመወዳደር ሊያደርጉት ከነበረው የቅድመ ምርጫ ፉክክር አግደዋቸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትራምፕ በድጋሚ ለዋይት ኃውስ ለመወዳደር ብቁ ናቸው ወይ የሚለውን ይወስናል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት፣ ዲሞክራቷ ቤሎውስ በተናጠል እርምጃ በመውሰድ የመጀመሪዋ የምርጫ አስፈፃሚ ሆነዋል። ቤሎውስ ትራምፕን ያገዷቸው የዩናይትድ ስቴትስ ሕገ-መንግስት ላይ የተቀመጠውን የአመፅ አንቅፅ በመጥቀስ ነው።

ውሳኔውን ተከትሎ የትራምፕ ምርጫ ዘመቻ ባወጣው መግለጫ የቤሎውስን ውሳኔ ለሜይን ግዛት ፍርድ ቤቶች በማቅረብ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አስታውቋል። መግለጫውበሰማያዊ ግዛቶች ውስጥ የሚገኙ ዲሞክራቶች በግደለሽነት እና ሕገ-መንግስታዊ ባልሆነ መንገድ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ስም ከምርጫ በማስወገድ፣ የአሜሪካ መራጮችን መብት እየገደቡ እንደሆነ የገለፀ ሲሆን "የምርጫ ስርቆት ሙከራ ሲደረግ እና የአሜሪካ ህዝብ የመምረጥ መብት ሲነፈግ እያየን ነው" ብሏል።

የቤሎውስ ውሳኔ የተላለፈው፣ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኮሎራዶ ግዛት ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ትራምፕ በግዛቱ በሚካሄድ ምርጫ እንዳይሳተፉ ያሳለፈውን ብይን ተከትሎ ነው።