በጦርነት በሚታመሰው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ወደፊት እየገፋ የሚገኘው የኤም23 ታጣቂ ቡድን ሌላ ከተማ መቆጣጠሩን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
እ.አ.አ ከ2021 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የጥቃት ዘመቻ ምስራቃዊውን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተቆጣጠረ ያለውን እና በቱትሲ ጎሳ የሚመራውን የኤም23 ቡድን ሩዋንዳ ትደግፋለች ስትል ኪንሻሳ ክስ ታቀርባለች። ሩዋንዳ በበኩሏ ክሱን አትቀበልም።
እሁድ እለት የኤም23 ተዋጊ ቡድን በሰሜን ኪቩ ግዛት የምትገኘውን ኪሩምባ ግዛት የተቆጣጠረ ሲሆን ቡድኑ በአካባቢው የትጥቅ ዘመቻ ከቀጠለበት ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ በሁከት ስትናጥ ቆይታለች። ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች የሚኖርባት ከተማ በስተሰሜን ወደ ቡተምቦ እና ቤኒ ስታሻግር በንግድ ማዕከልነት ትታወቃለች።
ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ባለስልጣን "ከትላንት ማታ ጀምሮ ከተማዋ በኤም23 እጅ በመውደቋ አዝነናል" ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እሁድ እለት ተናግረዋል። ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሲቪል ማኅበረሰብ መሪም ታጣቂዎቹ "አብዛኞቹ በእግር፣ ሌሎቹ ደግሞ በመኪና" ሆነው መግባታቸውን ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ እሁድ እለት ነዋሪዎቹን ሰብስበው ያነጋገሩ ሲሆን ወደ ቡቴምቦ እና ቤኒ እንደሚገቡ እና ቀጥሎ መዳረሻቸው የኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ እንደሚሆን መናገራቸውን ከስብሰባው ተሳታፊዎች አንዱ ከአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጋር በስልክ ባደረገው ቃለመጠይቅ ተናግሯል።