የሊቢያ ድንበር ጠባቂዎች በደርዘን የሚቆጠሩ እና፣ በቱኒዚያ ባልሥልጣናት በረሃ ላይ ተጥለናል ያሉ የአፍሪካ ፍልሰተኞችን መታደጋቸውን አስታውቀዋል። ሴቶች እና ሕጻናትም እንደሚገኙበት ታውቋል።
የቱኒዚያ ባለሥልጣናት ካለ ውሃ ምግብ እና መጠለያ በረሃ ላይ አምጥተው እንደጣሏቸው ፍልሰተኞቹ ለዜና ሰዎች ተናግረዋል።
ሙሳ ካሊድ የተባለ ፍልሰተኛ ለአሶስዬትድ ፕረስ እንደተናገረው፣ የቱኒዚያ የጸጥታ ኃይሎች የግል ንብረቱን ከወረሱ በኋላ፣ ቁጥቋጥ በሚበዛበት በረሃ ላይ አምጥተው ጥለውታል። በቱኒዚያ ፖሊስ መደብደቡን እና በዚህም ጭንቅላቱ እና እጁ እንደተጎዳ ተናግሯል። የሊቢያ ባለሥልጣናት መጠለያ እንዲሰጡት ሙሳ ተማጽኗል።
የሙቀት መጠኑ ከ40 ዲግሪ ሴልሲየስ በላይ በሆነበት አካባቢ ስድስት ወንዶችን እና ሌሎች በቡድን የነበሩ ሴቶችን ባለፉት ጥቂት ቀናት ማግኘታቸውን የሊቢያ ድንበር ጠባቂዎች ጨምረው አስታውቀዋል።