ደርና በተሰኘች የሊቢያ ምሥራቃዊ ከተማ በደረሰ ከባድ ጎርፍ፣ ሕይወታቸውን ያጡ 700 ሰዎች ቀብር ተፈጸመ። ቁጥራቸው በ10ሺሕ የሚገመቱ ደግሞ ያሉበት አልታወቀም፤ ተብሏል። አንዳንድ ምንጮች፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደ ሞቱ እየገለጹ ናቸው።
የአሶሺዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ከካይሮ እንደዘገበው፣ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አስከሬኖችን እየሰበሰቡ በመኾናቸው፣ የሟቾቹ ቁጥር ከተጠቀሰውም በላይ ሊኾን ይችላል።
ከሜዲትሬንያን ባሕር የተነሣውና ዝናም የቀላቀለው “ዳንኤል” የተሰኘው አውሎ ነፋስ፣ በምሥራቅ ሊቢያ በሚገኙ ከተሞች ከፍተኛ ውድመት እንዳስከተለ ተገልጿል። በአንዳንድ ቦታዎች፣ መንደሮች በጠቅላላ በጎርፉ ተጠራርገው ተወስደዋል።
የአገሪቱ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ሓላፊ እንዳሉት፣ 10ሺሕ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም። የአምቡላንስ እና የድንገተኛ አደጋ ባለሥልጣን በበኩሉ፣ በደርና ከተማ 2ሺሕ300 ሰዎች እንደሞቱ ቢያስታውቅም፣ ግምቱ በምን ላይ እንደተመሠረተ አልገለጸም፤ ሲል፣ አሶሺዬትድ ፕረስ በዘገባው አመልክቷል።