የሊብያው ጦርነት ተባብሷል

  • ቪኦኤ ዜና
የሊብያው አፈንጋጭ ጄነራል ኻሊፋ ሃፍታር ኃይሎች ዋና ከተማዪቱን ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ውጊያ ከጀመሩ ወዲህ እጅግ ብርቱው የተባለ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሊብያ ልዑክ ጋሳን ሳላሜ አስታወቁ።

በዛሬው ውጊያ ቢያንስ አምስት ሲቪሎች መገደላቸውንና ቁጥሩ የበዛ ሰው መቁሰሉን የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱያሪክ ተናግረዋል።

የተባባሰው የከባድ መሣሪያዎች ተኩስ እና ቦታ ያልለየ ድብደባ የሲቪሎችን መኖሪያ አካባቢዎች፣ ትምህርት ቤቶችንና መሠረተ ልማቱን እያወደሙ መሆናቸውን የገለፁው ሊብያ የሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት ድጋፍ ሰጭ ልዑክ ክሥ አሰምቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ ሰብዓዊ እርዳታ እና አገልግሎቶች በውጊያው አካባቢ ለተጠመዱ አካባቢዎች እንዲደርሱ የዋና ፀሐፊው ልዩ ልዑክ ጋሳን ሳላሜ ለዓለምቀፍ አሸማጋዮች አቤቱታ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል ብለዋል፡፡

ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲረግብና ተኩስ እንዲቆም ለማድረግ የታሰበ የውሣኔ ረቂቅ በዚህ ሣምንት ለማውጣት የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እያሰበ መሆኑ ታውቋል።

ሊብያን ለረዥም ዓመታት የገዟት ሞአማር ጋዳፊ የዛሬ ስድስት ዓመት በኃይል ከወደቁ ወዲህ ሃገሪቱ በቀውስና በሁከት እንደተዋጠች ነች።