በላይቤሪያ በአንድ የወርቅ ማዕድን ቁፋሮ ላይ በደረሰ አደጋ 13 ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች በናዳው ሥር ተቀብረው ሊሆኑ እንደሚችሉ ተዘግቧል።
የአገሪቱ የአደጋ መከላከያ ቢሮ እንዳስታወቀው፣ 25 የሚሆኑ ማዕድን አውጪዎች የአደጋው ሰለባ ሆነው የነበረ ሲሆን፣ አራት የሚሆኑት በሕይወት ተገኝተዋል።
በዓለም ካሉ እጅግ ደሃ አገራት ተርታ በምትመደበው ላይቤሪያ፣ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ቦታዎች ባህላዊ የወርቅ እና የአልማዝ አውጪዎች ሕይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ቁፋሮ ላይ ይሰማራሉ።
ባለፈው ጥር በማሊ በተከሰተ ተመሳሳይ አደጋ 60 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በላይቤሪያም ከአራት ዓመታት በፊት አንድ የማዕድን ጉድጓድ ተንዶ 50 ሰዎች ሞተዋል።