ምክትል ፕሬዚዳንት ጆዜፍ ቦአካዪ፣ ወይስ የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊአ? ለአሥራ ሁለት ዓመታት አገልግለው ሥልጣን እያስረከቡ ያሉትን የአሁኗን ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን የሚተካው ከሁለቱ ዕጩዎች አንደኛው ነው።
ለማንኛውም ቆጠራው እየተካሄደ፣ ለሁለቱም የተሰጡ ድምፆች አንዱ በአንዱ ላይ እየተደመረ፤ ቁጥሩም ለሁለቱም እያሻቀበ ነው። የቀድሞው የጎል ሱሰኛ ዊአ ግን አሸንፌአለሁ እያለ ነው። “በጣም ተደስቻለሁ፤ እንደማሸንፍ አውቃለሁ። ከሽንፈት ጋር ጉርብትና የለኝም። የዛሬው ድሌ የሚያጠራጥር አይደለም፤ አሸንፋለሁ” ብሏል።
ጆርጅ ዊአ ከላይቤሪያዊያን የአብዛኞቹ ድምፅ የእርሱ እንደሆነ ነው የሚናገረው።
ይሁን እንጂ ተቺዎች 51 ዓመቱን ዘንድሮ በነደፈው ዊአ ብዙ ምቾች አይሰማቸውም፤ የተጨበጠ የፖለቲካም ሆነ የአስተዳደር ልምድ የለውም።
የቦአካዪ ተቀናቃኞች ደግሞ የራሣቸው መከራከሪያ አላቸው። የሰባ ሦስት ዓመቱ ዕጩ የፕሬዚዳንት ሰፍሊፍ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበሩባቸው ዓመታት እምብዛም የሚያጠረቃ ተግባር ፈፅመው አልታዩም ባይ ናቸው።
የድምፅ አሰጣጡ ይህ ነው የሚባል የገዘፈ ችግር ሳይታይበት መካሄዱንና መጠናቀቁን የቀድሞውን የናይጀሪያ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ሌሎችም የታከሉበት ዓለምአቀፍ የታዛቢዎች ቡድን መስክሯል።
“መቼም አንድ ሰው ማሸነፍ አለበት። ያ ሰው ደግሞ ላይቤሪያዊ ነው። የሚሸነፈውም ሰው ላይቤሪያዊ ነው። ካሸነፍክ ታከብረዋለህ፤ ስታከብረው ደግሞ በብሄራዊ ደረጃ ነው የምታከብረው። ምክንያቱም የሁሉም ፕሬዚዳንት ነህና። ከተሸነፍክም ሽንፈትህን በክብር ትቀበላለህ” ብለዋል ሚስተር ጆናታን።
የትናንቱ ድምፅ እጅግ የተቀራረበ በመሆኑ ውጤቱን በይፋ ለማሳወቅ ምናልባት ጥቂት ቀናት መጠበቅ ሳያስፈልግ እንደማይቀር ቆጣሪዎቹ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ሁለም ነገር እስከአሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ ላይቤሪያ በሰባ ዓመታት ውስጥ የምታየው የመጀመሪያው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይሆናል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5