በደቡብ ዩክሬን የሩሲያ ሚሳይል ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል በርካቶች ቆሰሉ

  • ቪኦኤ ዜና

ሩስያ፣ ዛሬ ኀሙስ ማለዳ፣ በደቡባዊ ዩክሬን ሚካይሎቭ ከተማ ውስጥ በአደረሰችው የሚሳይል ጥቃት፣ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች 23 ሰዎች ቆስለዋል፡፡

ሩስያ፣ ዛሬ ኀሙስ ማለዳ፣ በደቡባዊ ዩክሬን ሚካይሎቭ ከተማ ውስጥ በአደረሰችው የሚሳይል ጥቃት፣ አንድ ሰው ሲገደል ሌሎች 23 ሰዎች ቆስለዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ፣ ሩስያ፣ ዛሬ ሌሊት በሚካይሎቭ ከተማ ላይ፣ በአራት ካሊበር ሚሳይሎች ጥቃት እንዳደረሰች ገልጸው፣ ሚሳይሎቹ የተወነጨፉት ከጥቁር ባሕር ላይ እንደኾነ ጠቁመዋል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ፣ ዩክሬን ከኅብረቱ አባላት እና አጋሮች ቃል ከተገቡላት የጦር መሣሪያዎች ውስጥ፣ 98 ከመቶው እንደደረሳት አመልክተዋል፡፡

የኔቶ ዋና ጸሐፊ፣ ዛሬ በብረስልስ በአደረጉት ጋዜጣዊ ጉባኤ፣ ኔቶ፥ ከዘጠኝ የሚበልጡ የዩክሬን ዐዲስ ታንከኛ ብርጌዶችን ማሠልጠኑንና ማስታጠቁን አስታውቀዋል፡፡

የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ እና ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ መወያየታቸው መልካም ዜና እንደኾነ የተናገሩት የኔቶ ዋና ጸሐፊ፣ ኾኖም ውይይቱ፣ የሩስያን ወረራ ላለማውገዝ ቻይና የያዘችውን አቋም አልቀየረም፤ ብለዋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት፥ ከፕሬዚደንት ሺ ጋራ በስልክ፣ “ረጅም ጊዜ የወሰደ ውጤታማ ውይይት” ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ወደ ኪቭ እና ቤጂንግ መልዕክተኞች ለመላላክ ቃል መገባባታቸውን አመልክተዋል፡፡ ይህም ሩስያ፣ ወረራዋን እንድታበቃ ለሚያደርግ የሰላም ድርድር ቅድመ ዝግጅት ሊኾን ይችላል ተብሎ ተወስዷል፡፡

የኹለቱ ፕሬዚዳንቶች ውይይት፣ ከሩሲያ ወረራ ወዲህ በይፋ የሚታወቅ የመጀመሪያው ውይይት ነው፡፡ በዚኹ ወቅት፣ ዩክሬን ወደ ቻይና የምትልካቸውን አምባሳደር መሠየሟ፣ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ያጠናክራል፤ ያሉት ዜሌንስኪ፣ ስለ ውይይቱ ግን በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

የቻይና መንግሥታዊ የዜና ማሠራጫዎች በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ሺ፣ በውይይቱ ላይ፣ ከኒውክሊየር ጦርነት የሚተርፍ እንደሌለ ማስጠንቀቃቸውንና ሁለቱ ወገኖች እንዲደራደሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ዘግበዋል፡፡