የመሬት ቅርምትና ኪራይ እሰጥ አገባ

የአፍሪካ ሃገሮች ለሌሎች ሃገሮች ወይም ኩባንያዎች ለተራዘመ ጊዜ የሚሰጧቸው መሬቶች ጉዳይ አነጋጋሪነት እየሰፋ ነው፡፡

መሬት ከሰዎች አሠፋፈር፤ ከሰብዓዊ፣ የዜግነትና የንብረት መብቶች፣ ከተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃና ልማት ጋር በጥብቅ የተቆራኘና የተሣሰረ በመሆኑ በየደረጃው የሚሰጠው ትርጉም የዚያኑ ያህል ጠበቅ ያለ ነው፡፡

የመሬት ይዞታን ሥሪት ከሚደነግገው መንግሥት በስንዝር መሬት ሙግት ሙሉ ዕድሜአቸውን እስከሚፈጁ ግለሰቦች አንገብጋቢና ትርጉም ያለው የሃብት ሁሉ ምንጭ እና የኢንቨስትመንትም መሠረት በመሆኑ ከቤት እስከ ዓለምአቀፍ መድረኮች አነጋጋሪ ነው፡፡

ከአካባቢያዊ ድንበር መጋፋት እስከ ወሰን ዘለል የግዛት ማስፋት ዘመቻዎችም የሚካሄዱት የበለጠ መሬት ያለው የበለጠ ኃይል ያለው በመሆኑም ነው፡፡

የዛሬ ቅዳሜ ፕሮግራማችን ርዕስም በዚሁ በመሬት ጉዳይ ላይ ያተኩራል፡፡ በተለይ የጊዜው አነጋጋሪ ርዕስ በሆነው በድንበር ዘለል የመሬት ኪራይ ወይም በሃሣቡ ተቀናቃኞች "መሬት መቀራመት" እየተባለ በሚጠራው አሠራርና በዙሪያውም ባሉት ንግግሮች ውስጥ የኢትዮጵያም ስም ደጋግሞ ይነሣል፡፡

የውጭ ባለኃብቶችና መንግሥት ለውስጥ የምግብ ፍጆታቸው ማሟያ ወደአፍሪካና ደቡብ ምሥራቅ እሥያ እየዘለቁ መሬት ይከራያሉ፤ በተቃዋሚዎቹ አባባል ይቀራመቱታል፣ ወይም ይዘርፉታል፡፡

አሠራሩ የሰፉ አስተያየቶች እንዲንሸራሸሩ፣ ውይይቶችም እንዲካሄዱ ሰበብ ሆኗል፡፡

በመሬት ኪራይ ወይም ቅርምቱ ጉዳይ ላይ ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉት አካላት መካከል በዩናይትድ ስቴትስ - ካሊፎርኒያ የሚገኘው ኦክላንድ ኢንስቲትዩት በሰባት የአፍሪካ ሃገሮች አድርጌአለሁ ያለውን ጥናት ውጤት የያዘ ሪፖርት በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተለያዩ አካላትን አስተያየት በተከታታይ የምናስተናግድ ሲሆን በዛሬው ዝግጅት የኢንስቱትዩተቱን ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የጥናቱ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት የአንስቱትዩቱ የፖሊሲ ዳይሬክተር አስተያየቶች ይቀርባሉ፡፡

ሙሉውን ዘገባ ያዳምጡ