አሜሪካ ለአፍሪካ ቀንድ ድርቅ መቋቋሚያ ተጨማሪ ድጋፍ ሰጠች

ፎቶ ፋይል፦ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዳድሌ ወረዳ ባዮሎው ቀበሌ አንዲት ሴት ከብቶቿን ወደ ወንዝ ዳርቻ እየመራች።

ከሃያ ሚሊየን በላይ ሰው ለምግብ፣ ለውኃና ለመድኃኒት እጥረት በተጋለጠባቸው ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ ውስጥ ለሚካሄዱ መርኃግብሮች የ200 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ እርዳታ መስጠቱን የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አስታወቀ።

በቀጣናው ለተራዘመ ጊዜ ዝናብ አለመጣሉ በ40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ ድርቅ ማስከተሉ ተዘግቧል።

አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ላይ እየታየ ያለውንና የሚሊዮኖችን ህይወት ለጉዳይ ያጋለጠውን ድርቅ ገፅታ የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ የሰብዓዊ ድጋፍ ጉዳዮች ቢሮ ረዳት አስተዳዳሪዋ ሳራ ቻርልስ ለጋዜጠኞች በኢንተርኔት አብራርተዋል።

“የድርቁ መደጋገምና ብርታት፣ እንዲሁም በአካባቢው እየታየ ያለው የእርዳታ ፍላጎት ማሻቀብ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም እጅግ ድኃ በሆኑ ማኅበረሰቦች ላይ ባልተመጣጠነ ሁኔታ እያደረሰ ያለውን አውዳሚ ጉዳት እያሳየ ነው። በተጎዱት አካባቢዎች አንድ ሚሊየን ተኩል እንስሳት አልቀዋል።

የኬንያ ሰሜናዊና የኢትዮጵያ ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎችን ጨምሮ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮው አቅርቦት መመናመን ለግጭቶች መከሰት ምክንያት ሆኗል። እጅግ አሳሳቢ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ለአጣዳፊ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል። ከሶማሊያ እየወጣ ያለ አስደንጋጭ ሪፖርት ታዳጊ ልጃገረዶች በምግብና ውኃ ለውጥ ለጋብቻ እየተሰጡ መሆናቸውን ይናገራል” ብለዋል ቻርልስ።

ለድርቁ ተጎጂዎች የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት እየሰጠ ያለው እርዳታ ከአሁኑ 200 ሚሊዮን ዶላር ጋር ወደ 360 ሚሊየን ማደጉን ሳራ ቻርለስ ገልፀዋል። ይሁን እንጂ በአካባቢው እያደረጉ ያሉትን ርብርብ ለማጠናከር የሚያስፈልጋቸው ወደ 4 ቢሊየን ተኩል ዶላር መሆኑን የሰብዓዊ ረድዔት ድርጅቶች አመልክተዋል።

ወደ ስድስት ሚሊየን ሰው የድርቁን ጉዳት እየሸሸ መሆኑንና ሶማሊያ ውስጥ ብቻ 3 ሚሊየን ሰው መፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል። የቢሮው ኃላፊ በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሁለት ሚሊየን ህፃናት በረሃብ ሊሞቱ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት እየተንቀሳቀሱ ያሉ ድርጅቶች በአካባቢው የፀጥታ ችግር ተዳምሮበት በተለይ ሁኔታው ትግራይ ውስጥ እጅግ አጣዳፊ መሆኑን እየገለፁ ነው።

ስለሆኔታው ያብራሩት ሳራ ቻርለስ “ትግራይ ውስጥ በተለይ ቢሮክራሲያዊ ማስተጓጎል፣ ግጭት፣ ሁከት፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ለመድረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔት እየተፈታተኑት ነው። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ አነስተኛ የእርዳታ አቅርቦት መግባቱንና ትናንትም ከብዙ ወራት በኋላ እርዳታ መቀሌ መግባቱን አይተናል”

ይዘንባል ተብሎ በተጠበቀው ጊዜም የጣለው ዝናብ እጅግ አነስተኛ መሆን የድርቁ ሁኔታና መዘዙ የባሰ እንዳይሆን አስግቷል።

ጥሩ ዝናብ ቢጥል እንኳ እስካሁን የተጎዳውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሰው ፈጥኖ እንዲያገግም ለማድረግ እንደሚከብድ የረድዔት ድርጅቶች እየተናገሩ ነው።