ዋሺንግተን ዲሲ —
ፈረንሳይ ኒስ ከተማ ውስጥ በስለት በተፈፀመ ጥቃት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን የሃገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
የኒስ ከተማ ከንቲባ ክሪስቲያን ኤስቶሮዚ በሰጡት መግለጫ በከተማዋ በሚገኘው ኖትረ ዴም ቤተ ክርስቲያን አጠገብ የደረሰውን ጥቃት በከተማዋ በሁለት ወር ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተፈፀመ የሽብርተኛ ጥቃት ሲሉ ገልጸውታል።
ከንቲባው እንዳሉትም አጥቂውን ፖሊሶች አቁስለውት በቁጥጥር ሥር አውለውት ህክምና እየተሰጠው እያለ በተደጋጋሚ “አላሁዋክበር" ይል ነበር ብለዋል።
የፈረንሳይ አቃብያነ ህግ ምርመራ ከፍተዋል።
በቅርቡም ሳሙኤል ፓቲ የተባለ መምህር አንገቱን ተቀልቶ መገደሉ የሚታወስ ሲሆን መምህሩን የገደለው የቼችኒያ ተወላጂ አጥቂ መምህሩ ለተማሪዎቹ የነብዩ መሃመድን የካርቱን ስዕል ለተማሪዎቹ በማሳየቱ ለመቅጣት ፈልጌ ነው ሲል ተናግሯል። የዛሬው ጥቃት ከዚያ ጋር ተያያዥነት ይኖረው እንደሆነ ለጊዜው ግልጽ አይደለም።
የፈረንሳይ ፖሊስ ምንጮች እንዳሉት በዛሬው ጥቃት የተገደሉ አንዲት ሴት አንገታቸው ተቀልቷል። የፈረንሳይ የፖለለቲካ ሰው ማሪን ሌ ፔይንም በጥቃቱ አንገቱ የተቀላ ሰለባ እንዳለ ጠቁመዋል።