በተባበሩት መንግሥታት ለሚደገፈውና በሄይቲ ለተሰማራው ልዑክ ተጨማሪ 600 የፖሊስ ዓባላትን እንደሚልኩ የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ዛሬ አስታውቀዋል።
በወሮበሎች በምትታመሰው ሄይቲ የተሰማራውን ዓለም አቀፍ ልዑክ እንድትመራ ኃላፊነት የወሰደችው ኬንያ በመጀመሪያው ዙር ሥምሪት 400 የፖሊስ ዓባላቶቿን ልካለች፡፡
የፖሊስ ዓባላቱ ከሥምሪት በፊት የሚሰጠውን ሥልጠና ማጠናቀቃቸውንና በሚቀጥለው ወር ለሥምሪት ዝግጁ እንደሚሆኑ ሩቶ ከሄይቲ ጊዜያዊ ጠቅላይ ምኒስትር ጌሪ ኮኒል ጋራ ሆነው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ኬንያ ወደ ሄይቲ የምትልከው የፖሊስ ኃይል እስከ 2ሺሕ 500 ሊደርስ እንደሚችል የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።