በኬንያ በከባድ ዝናብ ግድብ ተደርምሶ የደረሰው የጎርፍ አደጋ በርካቶችን ገደለ

  • ቪኦኤ ዜና

ግድቡ ከተደረመሰ በኋላ ነዋሪዎች አካባቢውን ለማፅዳት እየሞከሩ በናኩሩ ወረዳ ማይ ማሂዩ ኬንያ እአአ ሚያዚያ 29/2024

በደቡብ ምዕራብ ኬንያ በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ግድብ ተደርምሶ ባስከተለው ጎርፍ ከ40 በላይ ሰዎች ሞቱ፡፡

በናኩሩ ወረዳ ማይ ማሂዩ አካባቢ የግድቡን መፍረስ ተከትሎ የተፈጠረው ድንገተኛ ጎርፍ በትንሹ 16 ቤቶችንም ጠራርጎ ሲወስድ በርካታ ጉዳቶችን አስከትሏል፡፡

የአካባቢው ነዋሪ ጆን ካሩንጉ ከጠዋቱ 2፡30 አካባቢ ግድቡ ፈርሶ ጎርፉ እየጨመረ ሲሄድ ነዋሪዎች መሸሻቸውን ተናግረዋል፡፡ ብዙ ህጻናት እና ጎልማሶችን ለማትረፍ የተቻለ ቢሆንም አንዳንዶቹ በሚያሳዝን ሁኔታ ተወስደዋል ብለዋል፡፡

የናይቫሻ ፖሊስ አዛዥ እስጢፋኖስ ኪሩይ በጎርፍ አደጋ 45 አስከሬኖች መነሳታቸውን እና 110 ሰዎች ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት የኬንያ ቀይ መስቀል ተጨማሪ ዝናብ እንደሚኖር አስጠንቅቆ ህዝቡ ሊከተል ስለሚችለው ጎርፍ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቦ ነበር።

በኬንያ ዝናብ መጣል ከጀመረበት መጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ በጎርፍ አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል።

በቀጠለው አደጋ ምክንያት የኬንያ መንግስት ቀውሱን ለመቆጣጠር እና ደህንነትን ለማስጠበቅ ትምህርት ቤቶችን እስከሚቀጥለው ሳምንት ዘግቷል።