በከባድ ዝናብ እና ጎርፍ በተመታችው ኬንያ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ በኮሌራ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዛሬ ረቡዕ አስታውቋል።
ለሳምንታት በጣለው ከባድ ዝናብ እና በተከተለው ጎርፍ ሳቢያ ክፉኛ በተጠቃው ታና ወንዝ በተሰኘው አውራጃ አካባቢ 44 ሰዎች በኮሌራ እንደተያዙ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።
ከዚህ በፊት የኮሌራ ወረርሽኝን ተቆጥጥረው እንደነበር ያስታወቁት በኬንያ የተመድ አስተባባሪ ስቲፈን ጃክሰን፣ ከመንግስት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋራ በመሆን ይህንንም ወረርሽኝ መቆጣጠር እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
በኬንያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ አብዱራማኔ ዲያሎ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ለተፈጠረው አስቸኳይ የጤና ችግር ምላሽ በመስጠት በኩል እንደሚተባበር አስታውቀዋል።
በኬንያ በተከሰተው ጎርፍ እስከ አሁን ወደ 238 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ 235 ሺሕ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
በምሥራቅ አፍሪካ በጎርፍ ምክንያት በድምሩ 400 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። ቀጠናው ከረጅም ጊዜ ድርቅ በተላቀቀበት ባለፈው ዓመት በተከሰተው ከባድ ዝናብና ጎርፍ፣ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ 300 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።