ኬንያ ከሕንዳዊው ባለጸጋ ጋራ የገባችውን የአውሮፕላን ማረፊያና የኃይል ስምምነት ሰረዘች

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል፦ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሀገራቸው ከህንዳዊው ባለጸጋ ጋውታም አዳኒ ጋራ የገባችውን ብዙ ሚሊዮን ዶላሮች የሚፈጅ የአውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ እና የሃይል ምንጭ ግንባታ ስምምነቶችን መሰረዛቸውን ዛሬ ሐሙስ አስታወቁ።

ሩቶ ይህን ያስታወቁት ዩናይትድ ስቴትስ ባለፈው ሳምንት በእስያ ከሚገኙት ባለጸጎች በአንዱ ላይ የጉቦ እና የማጭበርበር ክስ መመስረቷን ካስታወቀች በኋላ ነው፡፡

ፕሬዝዳንቱ ውሳኔው የተላለፈው “በእኛ የምርመራ ተቋማት እና አጋር ሀገራት በቀረበው አዲስ መረጃ ላይ ተመስርቶ ነው” ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዩናይትድ ስቴትስን ለይተው አልገለጹም፡፡

የአዳኒ ቡድን በዋና ከተማዋ ናይሮቢ የሚገኘውን የኬንያ ዋና አውሮፕላን ማረፊያ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት በመፈራረም ሂደት ላይ ሲሆን፣ በስምምነቱ መሠረት ተጨማሪ ማኮብኮቢያ እና መናኻሪያ በመገንባት በምትኩ ለ30 ዓመታት አየር መንገዱን የማስተዳደር ሥራ እንዲወስድ የታሰበ ስምምነት ነው፡፡

ብዙ የተተቸው ስምምነት በኬንያ ጸረ-አዳኒ ተቃውሞን የቀሰቀሰ ሲሆን "የሥራ ሁኔታ ማሽቆልቆል እና አንዳንድ ቦታዎችም ላይ ከሥራ መፈናቀልን ያመጣል" ያሉ የአውሮፕላን ማረፊያ ሠራተኞችን የሥራ ማቆም አድማ አስከትሏል፡፡

የአዳኒ ቡድን የምሥራቅ አፍሪካ የንግድ መናኻሪያ በሆነችው ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመዘርጋት የሚያስችል ስምምነት አግኝቷል።

የኃይል ሚኒስትሩ ኦፒዮ ዋንዴ ለፓርላማው ኮሚቴ በሰጡት ቃል "በኬንያ በኩል ይህንን ስምምነት በመፈረም ሂደት ምንም አይነት የጉቦ ወይም የሙስና አድራጎት አልተፈጸመም" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ህግ በዚህ ሳምንት በመሠረተው ክስ አዳኒ ህንድ ውስጥ የሚገነባው ግዙፍ የጸሐይ ሓይል ፕሮጀክት በጉቦ የተመቻቸ ነው የሚል ውንጀላ የቀረበበት ሲሆን ይህንኑ በግንባታ ፕሮጄክቱ መዋእለ ነዋይ ካፈሰሱ ባለሃብቶች ደብቆ አጭበርብሯቸዋል ብሏል፡፡ አዳኒ የሀሰት የፋይናንስ መረጃዎችን በማቅረብ ለማጭበርበር አሲረዋል ተብለው ተከሰዋል፡፡