“እጅግ የተከበሩ እንደራሴና የመንግሥት ሰው፤ እጅግ ኩሩ ተዋጊና አርበኛ፤ እራሱን አሳልፎ የሰጠ የሕዝብ አገልጋይ...” አሜሪካ ከትናንት በስተያ ቅዳሜ፤ ነኀሴ 19/2010 ዓ.ም. አጣች።
ይህንን ውዳሴና ሞገስ እያዘነቡ ያሉት ሴናተር ጃን መክኬንን በቅርብ የሚያውቁ፣ አብረዋቸው የዋሉ፤ የኖሩና የሠሩ ወዳጆችና በግራም በቀኝም ያሉ ባልደረቦቻቸው ናቸው።
ጃን መክኬን በ81 ዓመት ዕድሜአቸው ከትናንት በስተያ አረፉ፤ በጠና የታመሙበት የአንጎል ደዌ ላለፉት ጥቂት ወራት ከለመዱትና አብዝቶም ከለመዳቸው አደባባይ ነጥሎ እቤት አውሏቸው ነበር።
በሕይወታቸው ማብቂያ ወራትና ሰሞናት ሁሉ ግን ስለሃገራቸው በብርታት፣ በሚታወቁበትም የፅናትና የነፃነት መንፈሳቸው መናገራቸውን አላቆሙም።
“እኛ የተባረክን ነን - አሉ መክኬን በቅርቡ ባደረጉት አንድ ንግግራቸው ላይ - የምንኖረው ሁሉም ነገር በሚቻልበት የነፃዎች ሃገር ውስጥ ነው።”
መክኬን በትረምፕ ዘመነ-አስተዳደር አስተውያለሁ ስላሏቸው ችግሮችም ትችትና ወቀሳቸውን በግላጭ ከመናገር አልተቆጠቡም።
የዩናይትድ ስቴትስ አድሚራል ልጅ ጃን መክኬን የባሕር ኃይሉ አብራሪ ሆነው በቪየትናም ጦርነት ወቅት በአየር ድብደባ ተልዕኮዎች ላይ ተሰልፈዋል፣።
በ1960 ዓ.ም. (በኢት.የዘ.አ.) ያርሯት የነበረች ጄት ይፋለሟቸው በነበሩ የሰሜን ቪየትናም ኃይሎች ተመታችና እርሣቸውም ጠላት እጅ ላይ ወደቁ። የጦር ምርኮኛ ሆነውም ለአምስት ዓመታት በስቃይ አያያዝና በእንግልት እንዲቆዩ መደረጋቸውን ታሪካቸው ይናገራል።
በ1994 ዓ.ም. ዩናይትድ ስቴትስ ላይ ከተፈፀመው የመስከረም አንድ ጥቃት በኋላም ምንም እንኳ መክኬን የአፍጋኒስታንና የኢራን ጦርነቶችን ቢደግፉም በሽብር ተጠርጣሪዎች ላይ ይካሄድ የነበረውን የስቃይ ምርመራና ዘዴዎች በብርቱ ሲቃወሙ ቆይተዋል።
ጃን መክኬን ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንትነት ሁለት ጊዜ ያልተሣኩ ውድድሮችን አድርገዋል። አንዴ ከጆርጅ ቡሽ (ሁለተኛ)፣ አንዴ ደግሞ ከባራክ ኦባማ ጋር።
በባራክ ኦባማ የመጀመሪያው ውድድር ወቅት ‘አረብ ናቸው’ የሚል ሃሜት ይናፈስ ነበርና ያንኑ ጉዳይ በአንድ የራሳቸው የምረጡኝ ዘመቻ መድረክ ላይ መክኬን ሲጠየቁ “የለም፤ ከእኔ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የማንግባባ ዜጋ፣ ጨዋ የቤተሰብ ሰው ናቸው” ብለው ስለተፎካካሪያቸው የሰጡት እማኝነት ብዙ ክብር አስገኝቶላቸዋል።
መክኬን እስካለፉ የሴኔቱ የጦር ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበርም ነበሩ።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5