በጃፓን በተጋጩ አውሮፕላኖች አምስት ሰዎች ሞቱ

የመንገደኞች አይሮፕላን በቶኪዮ ሃኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ የተከሰተው አደጋ

· ርዕደ መሬት አደጋው የሞቱት 48 ሰዎች ደርሷል

አንድ የመንገደኞች አይሮፕላን በቶኪዮ ሃኔዳ አውሮፕላን ማረፊያ ማኮብኮቢያ ላይ ከጃፓን የባህር ጠረፍ ጠባቂ አውሮፕላን ጋር ተጋጭቶ፣ በእሳት ነበልባል መያያዙን ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ኤን ኤች ኬ ቲቪ እንደዘገበው በጃፓን አየር መንገድ አውሮፕላን JAL-516 ውስጥ ከነበሩት መካከል 379 ተስፋሪዎች፣ አውሮፕላኑ ሙሉ በሙሉ በእሳት ከመቃጠሉ በፊት በሰላም ወጥተዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

የጃፓን የባህር ጠረፍ ጠባቂ የአውሮፕላኑ አብራሪ አምልጧል ብሏል።

ኤን.ኤች.ኬ እንደዘገበው አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ አምስቱ የበረራ አባላት ሞተው ተገኝተዋል።

የአካባቢው ቴሌቪዥን እንዳሳየው በማኮብኮቢያው ሜዳ ላይ ከነበረው አውሮፕላን በስተጎን በኩል ከፍተኛ እሳት እና ጭስ ሲወጣ የታየ ሲሆን ፣ ወደክንፉ ዙሪያ አካባቢ የተሻገረው እሳት ከአንድ ሰዓት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ አውሮፕላኑ ክፍሎች መዛመቱ ታይቷል፡፡

ኤን ኤች ኬ ቲቪ እንዳስታወቀው አውሮፕላኑ በሳፖሮ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው ከሺን ቺቶስ አየር ማረፊያ ወደ ሃኔዳ የበረረው ኤርባስ A-350 ነው።

የባህር ዳርቻ ጠባቂው አውሮፕላን ትናንት ሰኞ በክልሉ ቢያንስ 48 ሰዎችን ለገደለው ርዕደ መሬት የእርዳታ እቃዎች ለማድረስ ወደ ኒጋታ ሊያቀና እንደነበር ተነግሯል፡፡

ሃኔዳ በጃፓን ውስጥ በጣም ከተጨናነቁ አውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ ሲሆን ለአዲሱ ዓመት በዓላት በርካታ ሰዎች እንደሚገለገሉበት ተነግሯል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም በምዕራብ ጃፓን ትናንት ሰኞ በደረሰው ተከታታይ ከባድ ርዕደ መሬት በትንሹ 48 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በሺዎች በሚቆጠሩ ህንፃዎች፣ ተሽከርካሪዎች እና ጀልባዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

ባለሥልጣናቱ ተጨማሪ የርዕደ መሬት አደጋ ወደፊት ሊመጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ትናንት ሰኞ ከሰዓት በኋላ በሬክተር ስኬል መለኪያ 7.6 መሆኑ የተነገረለት ርዕደ መሬት አካባቢውን ካመታ ከአንድ ቀን በኋላ የኢሺካዋ ግዛት እና በአቅራቢያው ያሉ አካባቢዎችን ማንቀጥቀጡ ተነግሯል።

በኢሺካዋ አርባ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ሌሎች 16 ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን በመኖሪያ ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ትክከለኛውን ጉዳት ወዲያውኑ መለየት አለመቻሉን ባለሥልጣናት አመልክተዋል፡፡

የጃፓን መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ወድመዋል።

አደጋውን ተከትሎ የውሃ፣ የመብራት እና የሞባይል ስልክ አገልግሎት አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች የተቋረጠ ሲሆን ነዋሪዎቹ በፈረሱት ቤታቸው እና የወደፊት እጣ ፈንታቸው ማዘናቸውን ገልጸዋል።