የጃፓን ምጣኔ ኃብት በ2.5 ከመቶ ቀንሷል

  • ቪኦኤ ዜና
የጃፓን ምጣኔ ኃብት ባለፈው የዓመቱ ሦስተኛ ሩብ ውስጥ በ2.5 ከመቶ ቀንሷል።

የጃፓን ምጣኔ ኃብት ባለፈው የዓመቱ ሦስተኛ ሩብ ውስጥ በ2.5 ከመቶ ቀንሷል።

ይህ በሐምሌ በነኀሴና በመስከረም ወሮች ውስጥ የታየው አጠቃላይ መኮማተር ባለፉ አራት ዓመታት ውስጥ በጃፓን ምጣኔ ኃብት ላይ ከደረሰው ማሽቆልቆል ሁሉ የበረታ መሆኑን ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ምንም እንኳ ቀደም ሲል የወጣው ትንበያ ምጣኔ ኃብቱ በ1.2 ከመቶ ሊዳከም እንደሚችል ይጠቁም የነበረ ቢሆንም የዛሬው ሪፖርት ያንን ሥጋት ከእጥፍ በላይ አሳድጎት ተገኝቷል።

ጃፓን ይህ መንሸራተት ያጋጠማት ፋብሪካዎች ማምረት እንዲያቆሙ ወይም ምርታቸውን እንዲቀንሱ ያስገደዱ የተፈጥሮ አደጋዎች በተከታታይ የደረሱባት መሆኑ እንዲሁም እየወረደ ከመጣው የግዥ ፍላጎትና የኩባንያዎች መዋዕለ-ነዋይ መቀነስ ጋር ተዳምረው መሆኑ ተገልጿል።

በዩናይትድ ስቴትስና በቻይና መካከል የተጫረው የንግድ ጦርነትም በጃፓን ምጣኔ ኃብት ላይ ያንን ያህል ባይበረታም ጫና ማሳደሩ ተጠቁሟል።

አጠቃላዩ የሃገር ውስጥ ምርትም ከቀደመው ሩብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በዜሮ ነጥብ ስድስት አሽቆልቁሏል።

ይሁን እንጂ ይህ ከዩናይትድ ስቴትስና ከቻይና ቀጥላ ሦስተኛዪቱ የዓለም ግዙፍ ምጣኔ ኃብት የገባችበት ፈተና ጊዜያዊ ነው የሚል ዕምነት እንዳላቸው የምጣኔ ኃብት አዋቆችና ተንታኞች እየተናገሩ ነው