ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ወስዳ የነበረውንና ‘ፀሐይ’ በመባል የምትጠራውን አውሮፕላን መመለሷን አስታወቁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በX የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ትላንት እንዳሰፈሩት፣ “ፀሐይን ከጣሊያን መንግሥት በመረከባችን ዛሬ ለኢትዮጵያውያን የክብር ቀን ነው” ብለዋል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1935 ዓ.ም በአንድ ጀርመን መሃንዲስ እና በኢትዮጵያውያን ትብብር ፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ የተሠራች አውሮፕላን መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በመልዕክታቸው አስታውሰዋል።
አውሮፕላኗ የፋሺት ጣሊያን መሪ ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኃይሎች ኢትዮጵያን በወረሩበት ወቅት እንደተወሰደች የታሪክ አጥኚዎች ይገልፃሉ።
የጣሊያን መከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ ግራጫ ቀለም ኖሯት የተሠራችው ባለአንድ ክንፍ አውሮፕላን የመጀመሪያ በረራዋን በታኅሣስ 1935 ዓ.ም ማድረጓን አስታውሶ "ልዩ ናሙና" ናት ሲል ጸሐይን ገልጿታል። ፀሐይ በወቅቱ በአጠቃላይ ለ30 ሰዓታት የበረረች ቢሆንም "ጣሊያን ከመግባቱ እና ከመውሰዱ በፊት፣ እ.አ.አ ከግንቦት 1936 ጀምሮ አዲስ አበባ ላይ ተትታ ነበር" ሲል አክሏል።
SEE ALSO: “ፀሐይ” ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰራችው ብቸኛዋ አይሮፕላን የት ናት?ከእ.አ.አ 1941 ጀምሮ በኢጣሊያን የአየር ኃይል ሙዚየም ውስጥ ለዕይታ ተቀምጣ እንደነበር ያመለከተው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተወስዳ ለዕይታ እንደምትቀርብ ቀን ሳይጠቅስ ማስታወቁን የኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ አመልክቷል።
አውሮፕላኗ ፀሐይ የሚለውን ስያሜ ያገኘችው ከቀዳማዊ ሀይለስላሴ ልጅ፣ ልዕልት ፀሐይ ነው።