ሜዲትሬንያን ባሕርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመሻገር በመሞከር ላይ የነበሩ ፍልስተኞች፣ ጀልባቸው ተገልብጦ አንድ ሕፃንን ጨምሮ ዘጠኙ ሲሞቱ፣ 15 የሚሆኑት ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን የጣሊያን የባሕር ጠረፍ ጥበቃ አስታውቋል።
ከላምፔዱሳ ደሴት 50 ኪ.ሜ. ላይ ማዕበል በማየሉ ትናንት ረቡዕ አደጋው ሲደርስ፣ ከማልታ የአደጋ ግዜ ሠራተኞች የትብብር ጥያቄ ደርሶት እንደነበር የጣሊያን የባሕር ጠረፍ ጥበቃ ጨምሮ ገልጿል።
ሃያ ሁለት ፍልሰተኞችን መታደጉን እንዲሁም አንድ ሕፃንን ጨምሮ የዘጠኝ ሰዎችን አስከሬን ማግኘቱን የባሕር ጠረፍ ጥበቃው አስታውቋል።
የሟቾቹ ዜግነት እስከ አሁን ያልተገለፀ ሲሆን፤ በቱኒዚያ፣ ማልታ እና ሲስሊ መካከል የምትገኘው ላምፔዱሳ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚሞክሩ ፍልሰተኞች የመጀመሪያ ማረፊያ ነች፡፡
በሌላ በኩል በላምፔዱሳ አቅራቢያ በትንሽ የእንጨት ጀልባ ላይ ሆነው ሲቀዝፉ የነበሩ 37 ፍልሰተኞችን ትናንት መታደጉን የባሕር ጠረፍ ጥበቃው ቡድን አስታውቋል።
በተያያዘ ዜና፣ ግሪክ የሶስት ታዳጊዎችን አስከሬን ማግኘቷን እና 19 ፍልሰተኞችን ደግሞ መታደጓን አስታውቃለች፡፡
ፍልሰተኞቹ ይጓዙበት የነበረው ጀልባ ከቋጥኝ ጋራ በመጋጨቱ አደጋው ሊደርስ እንደቻለ ተነግሯል።
ከአፍሪካ፣ እስያ እና መካከለኛው ምሥራቅ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ለሚሹ ፍልሰተኞች ሌላዋ አማራጭ የሆነችው ግሪክ፣ ከ እ.አ.አ 2015 ወዲህ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልሰተኞች በደሴቶቿ ተቀብላለች፡፡