ኢትዮጵያ፣ እሥራኤላዊውን በንግድ ሥራ ተዳዳሪ ግለሰብ ሜናሽ ሌቪይን ከእሥር ፈታች። መረጃውን ይፋ ያደረጉት፣ ሌቪይ እንዲፈታ አንድ የልዑካን ቡድን በመምራት ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው፣ መንግሥት በሌቪ ላይ የመሰረተውን ክስ እንዲሰርዝ ጫና ያደረጉት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አባል ክሪስ ስሚዝ ናቸው።
ዋሺንግተን ዲሲ —
ዜናውም በቅድሚያ ይፋ የሆነው፣ ትናንት ሐሙስ በወጣውና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚታተመው በእሥራኤሉ ‘Jerusdalem Post’ ጋዜጣ ላይ መሆኑ ታውቋል።
ከገንዘብ ወንጀል ጋር በተያያዘ ክስ እአአ በ2015 የታሰረው ሌቪ፣ ከመታሰሩ አስቀድሞ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በእሥራኤሉ የማዕድን አሰሳና ቁፋሮ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለሰባት ዓመታት ሲሰራ እንደነበር ታውቋል።
ሌቪስ እንደታሰረ ሰሞን አዲስ አበባ ውስጥ የታተመው ፎርቹን ጋዜጣ እንደዘገበው፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ሌቪስን ያሰሩት በጉቦ፣ በቀረጥ ወይም ግብር ማጭበርበር እና በብዙ ሚሊዮን ዶላር በሚገመት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀል እንደሆነም ተገልጧል።
በሃምሳ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ሌቪስ፣ የቀረበበት ክስ ሀሰት መሆኑን ቢያስተባብልም የተፈረደበት ግን ችሎት ሳይቀርብ መሆኑ ተገልጧል። ወህኒ በነበረበት አራት ዓመት ጊዜም፣ ሌቪ በሌላ እሥረኛ በጭካኔ በመደብደቡ፣ ለልብ ህመም መጋለጡ ተመልክቷል።