የእሥራኤል የጦር ጄቶች በምሥራቃዊ የሦርያ ግዛት ላይ ድብደባ መፈፀማቸው ተገለፀ

  • ቪኦኤ ዜና

የእሥራኤል የጦር ጄቶች ዛሬ ማለዳ ላይ በምሥራቃዊ የሦርያ ግዛት ላይ ድብደባ ፈፅመዋል። እሥራኤል ጥቃቱን የፈፀመችው የኢራን መሣሪዎችን ለማከማቸትና ለመትከል አገልግሎት ሲሰጥ በነበሩ ቦታዎች ላይ እንደሆነና ድብደባው የተካሄደው ዩናይትድ ስቴትስ ለእሥራኤል ባቀበለችው መረጃ መሠረት መሆኑን አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ የስለላ ባለሥልጣን የጠቀሰው የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ጠቁሟል።

የዛሬዎቹ ድብደባዎች የተፈፀሙት በዴር ኤል ዘር፣ በማያዲን እና በቡካማል ከተሞች ይዞታዎች ላይ መሆኑን የሶሪያ መንግሥታዊ የዜና ወኪል/ሳና/ ዘግቧል።

የጦርነቱን ሁኔታ እየተከታተለ ሪፖርት የሚያወጣው የሶሪያ የሰብ ዓሚ መብቶች ቃፊር ቡድን ቢያንስ 18 ድብደባዎች መካሄዳቸውንና ቁጥሩ ከ23 የማያንስ ሰው መገደሉን አስታውቋል።