እስራኤል በሁለቱ ቀናት ባደረሰቻቸው የአየር ጥቃቶች 558 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ የጤና ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ዛሬ ማክሰኞ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ላይ በተደጋጋሚ የአየር ድብደባ አካሂዳለች። ጥቃቶቹ ኢላማ ያደረጉት ወደሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶች የሚተኩሱትን ጨምሮ በርካታ የሄዝቦላ ተዋጊዎችን መሆኑን አመልክታለች።
ሄዝቦላ በበኩሉ ዛሬ ማክሰኞ የእስራኤል ወታደራዊ ሠፈሮች ላይ ያነጣጠረ የሮኬት ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኮምሽን (ዩኤንኤችሲአር) ቃል አቀባይ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል በሊባኖስ በብዙ አስር ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ከመኖሪያው እንዲሰደድ መገደዱን ገልጸው ከቀዬው የሚፈናቀለው ሰው ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል ብለዋል። ቃል አቀባዩ ማቲው ሳልትማርስ ሁኔታውን "እጅግ አሳሳቢ" ሲሉ ገልጸውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኅላፊው ቮልከር ተርክ በበኩላቸው "በቀጣናው ተሰሚነት ያላቸው ሁሉ ዓለም አቀፍ ሕግጋት እንዲከበሩ የተቻላቸውን ያድርጉ" ሲሉ ተማጽኖ አቅርበዋል።
በግጭቱ መባባስ የተነሳ የፈረንሳይ አየር መንገድ፥ የካታር አየር መንገድ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አየር መንገድ ኢቲሃድን ጨምሮ የተለያዩ አየር መንገዶች ቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ መግባትም ሆነ መነሳት አቁመዋል።