የእስራኤል ጦር በደቡብ ሊባኖስ ባካሄደው ጥቃት የሂዝቦላህን የተዋጊ አዛዥ መገደሉን ዛሬ ሐሙስ አስታውቋል። በጥቃቱ የተገደለው የተዋጊ አዛዥ ሁሴን አዋዳ እንደሚባል የገለጸው ጦሩ፣ ወደ እስራኤል ለሚተኮሱ ሚሳይሎች ተጠያቂ መሆኑንም ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል የሂዝቦላህ ታጣቂዎች ለሚገኙባቸው አካባቢዎች ቅርበት አላቸው ባለቻቸው ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች አካባቢያቸው ጥለው እንዲወጡ አዲስ ትዕዛዝ አስተላልፋለች። እስራኤል እንዲህ ያሉ ትዕዛዞች የምታስተላልፈው የአየር ጥቃቶችን ከማካሄዷ ቀደም ብላ ነው።
እስራኤል ትዕዛዙን ካስተላለፈችባቸው አካባቢዎች ውስጥ፣ በሊባኖስ ቤካ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙት ሳራይን፣ ታምኒን እና ሳፋሪ የተሰኙ አካባቢዎች ይገኙበታል።
እስራኤል ትላንት ረቡዕ በደቡባዊው ከተማ ናባቲህ ባካሄደችው የአየር ጥቃት ከንቲባውን ጨምሮ 16 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ50 በላይ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።