እስራኤል በሃማስ ተይዞ የቆየ ሌላ አንድ ታጋች አስለቀቅች

  • ቪኦኤ ዜና
የ52 ዓመቱን ካይድ ፋርሃን አልካዲን በጋዛ በሃማስ ታጣቂዎች ታግቶ የነበረው።

የ52 ዓመቱን ካይድ ፋርሃን አልካዲን በጋዛ በሃማስ ታጣቂዎች ታግቶ የነበረው።

ሃማስ ባለፈው መስከረም ወር መገባደጂያ አስደንጋጭ ጥቃት ባደረሰበት ወቅት ተይዘው ከተወሰዱት ቁጥራቸው 250 የሚደርሱ ሰዎች መካከል የሆኑ አንድ ሌላ ታጋች ማስለቀቋን እስራኤል በዛሬው ዕለት አስታውቃለች።

የ52 ዓመቱን ካይድ ፋርሃን አልካዲን አስረኛ ወሩን በያዘው የሁለቱ ወገኖች ጦርነት መሰንበቻውን ደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ ውስጥ ባካሄደው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት መታደጉን ያመለከተው የእስራኤል ጦር በአካባቢው ካለ አንድ የመተላለፊያ ዋሻ አቅራቢያ እንዳገኛቸው ቢያመለክትም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥቧል።

በኪቡትዝ ማጌን የምግብ ማሸጊያ ፋብሪካ በጥበቃ ሥራ ተሰማርተው ያገለግሉ የነበሩት አልካዲ በመስከረም 26ቱ የሃማስ ጥቃት ታግተው ከተወሰዱት በርካታ ከግብርና ጋር የተዛመዱ ሥራዎች የሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል አንዱ ከሆነው የእስራኤሉ አረብ ቤድዊን ሕዳጣን ማሕበረሰብ ናቸው። አልካዲ የሁለት ሚስቶች ባል እና የ11 ልጆች አባት መሆናቸው ታውቋል። አልካዲ “በአሁኑ ወቅት በተረጋጋ የጤና ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” ያለችው እስራኤል “ለተጨማሪ የጤና ምርመራ ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል” ስትል አክላለች።

የእስራኤሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ቻናል 12 የአልካዲን ከታገቱበት የመለቀቅ ዜና የሰሙ የቤተሰባቸው አባላት ግር ተሯሩጠው ወደ ሆስፒታሉ ሲገቡ አሳይቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁንም ድረስ ቁጥራቸው 110 የሚደርሱ ታጋቾች ያለመለቀቃቸውን እና ከነዚህም ውስጥ አንድ ሶስተኛው ህይወታቸው አልፏል ብላ የምታምን መሆኗን እስራኤል አመልክታለች። ከዚህ የተቀሩት ሁለቱ ወገኖች ባለፈው የህዳር ወር በደረሱት ለአንድ ሳምንት የዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ባደረጉት የእስረኞች ልውውጥ መለቀቃቸው ይታወሳል።

በርካታ ፍልስጤማውያን የተገደሉባቸውን ሁለት ወታደራዊ ዘመቻዎች ጨምሮ፤ እስራኤል በወሰደቻቸው ወታደራዊ እርምጃዎች ስምንት ታጋቾችን አስለቅቃለች። ሃማስ በበኩሉ በእስራኤል በፈጸመቻቸው የአየር ድብደባዎች እና ባልተሳኩ ሙከራዎቿ በርካታ ታጋቾች ተገድለዋል ይላል።