እስራኤል የዋናውን ጋዛ ሆስፒታል ኃላፊ ለቀቀች

  • ቪኦኤ ዜና

ከህዳር ወር ጀምሮ በእስራኤል ወታደሮች ተይዘው የነበሩት የአል-ሺፋ ሆስፒታል ዳይሬክተር መሐመድ አቡ ሰልሚያ ከሌሎች እስረኞች ጋር ከእስር ከተፈቱ በኋላ ዘመዶቻቸው በደቡባዊ ጋዛ ሰርጥ በካን ዮኒስ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል አቀባበል አድርገውላቸዋል፤ እአአ ሐምሌ 1/2024

እስራኤል ለሕክምና ወደ ጋዛ እንዲመለሱ ከለቀቀቻቸው በርካታ ፍርስጤማውያን እስረኞች መካከል የጋዛ ዋና ሆስፒታል ኃላፊ እንደሚገኙበት ተገለጸ።

ከሕዳር ወር ጀምሮ እስር ላይ የነበሩት መሐመድ አቡ ሰልሚያ ጋዛ የሚገኘው ሺፋ ሆስፒታል ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ እስራኤል ሐማስ ሆስፒታሉን እንደማዛዣ ማዕከል እየተጠቀመበት ነው በማለት በተመሳሳይ ወር ሆስፒታሉ ላይ ወረራ አካሂዳ ነበር።

የሆስፒታሉ ባለስልጣናት በበኩላቸው የእስራኤልን ውንጀላ ውድቅ በማድረግ፣ እስራኤል ታካሚዎችን እና ለመጠለያ ወደ ሆስፒታል የመጡ ፍልስጤማውያንን አደጋ ላይ ጥላለች ሲሉ ከሰዋል።

የእስራኤል የቀኝ አክራሪ ብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ጊቪር የአቡ ሴልሚያን መለቀቅ ተችተው በኤክስ ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት "ደህንነትን አሳልፎ መስጠት ነው" ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጦር፣ በደቡባዊ የጋዛ ክፍል፣ ድምበር አቅራቢያ ከምትገኘው ካን ዩነስ ታጣቂዎች ለተኮሱት 20 ሚሳይሎች ምላሽ ለመስጠት ጥቃቶች መፈፀሙን አስታውቋል። ከተተኳሾቹ ውስጥ የተወሰኑትን ማምከኑን ያስታወቀው ጦሩ የተቀሩት በደቡባዊ የእስራኤል ክፍል መውደቃቸውን ጠቅሷል።

ከጋዛ በተጨማሪ እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በርካታ መንደሮች ውስጥ የሚገኙ የሂዝቦላህ ታጣቂዎችን ዒላማ ያደረገ የአየር ጥቃትም አካሂዳለች። እስራኤል በሂዝቦላህ ላይ የከፈተችው መጠነ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ ግጭቱን በቀጠናው ሊያስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት የገባቸው ዩናይትድ ስቴትስ እና ሌሎች ሀገራት፣ ጦርነቱ ተባብሶ እንዳይቀጥል አስጠንቅቀዋል።